የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ የውድድር ግብዣ ቀረበለት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እ.ኤ.አ. በ1994 በሩዋንዳ ቱትሲ ህዝቦች ላይ የተደረገው የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን ለማስታወስ በሚደረገው የመታሰቢያ ውድድር እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቦለታል።

የሩዋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይህንን የመታሰቢያ ውድድር እ.ኤ.አ. በ2015 ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገ ሲሆን በውድድሩም ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ ተሳታፊዎች ነበሩ። የዘንድሮ ውድድር ከግንቦት 24 እስከ 27 ድረስ በኪጋሊ የሚደረግ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ለ13 የአፍሪካ ሃገራት ጥሪ በማድረግ የተሳትፎ ማረጋገጫ መልስ እየተጠባበቀ ይገኛል። በውድድሩ እንዲሳተፉ ጥሪ የቀረበላቸውም ሃገራት ሞሮኮ፣ ጊኒ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቶጎ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሊብያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋቦን፣ ላይቤሪያ፣ ጋና፣ ኬንያ እና ናይጄሪያ ናቸው።

ዘንድሮ ካለፈው ጊዜ በተለየ በውድድሩ ለመሳተፍ ወደ ሩዋንዳ የሚመጡ ቡድኖች ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ በራሳቸው መሸፈን እንደሚኖርባቸውም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

ሩዋንዳ ውድድሩን በዘር ማጥፋቱ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ከማስታወስ በተጨማሪ በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ባንጉይ ላይ ለምታደርገው ጨዋታ ዝግጅት የምትጠቀመው ይሆናል።

በውድድር ግብዣው ዙርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያለው ነገር ባይኖርም መርሀግብሩ ግንቦት 26 ቀን አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ ቀጠሮ ከተያዘለት የኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች የወዳጅነት ጨዋታ የሚጋጭ በመሆኑ ጥያቄውን ተቀብሎ በውድድሩ ላይ የመሳተፍ ዕድሉ ጠባብ ይመስላል።

1 Comment

  1. ethiopia weste eger koas ayasfelegem.mikiniyatum hulem wancha yemezegajew le Giorgi’s bicha New.beyet hager New 3 chaweta eyekere be temesasaye seat chewata yemederegew wesha yehone federation.weyem ye Addis abeba kileboch endaywerdu tasebo yemeta ekid new. Wesha federation

Leave a Reply