ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ውድድር – ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ

ቀን – ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2009

ሰአት – ምሽት 12:00

ቦታ – ሉካስ ሞሪፔ ስታድየም

ቀጥታ ስርጭት – ሱፐር ስፖርት ፣ ቢኢን ስፖርት

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ የምድብ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት ሲደረጉ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ምድብ ድልድሉ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአምናው ባለ ድል ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ይገጥማል፡፡ የመጀመርያ የምድብ ጨዋታ እንደመሆኑም ሶከር ኢትዮጵያ በሁለቱም ቡድኖች ዙርያ ሰፋ ያለ ዳሰሳ ይዛላችሁ ቀርባለች፡፡

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ

የ2016 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የውድድር አመቱን በተደበላለቀ አቋም እና ውጤት ጀምሯል፡፡ በ2016 ከሌላኛው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስ በመቀጠል የአህጉሪቱን ትልቁን የክለቦች ዋንጫ ማሸነፍ የቻለ ሁለተኛው የደቡብ አፍሪካ ክለብ የሆኑት ‘ብራዚሎቹ’ በመጋቢት ወር በተደረገው የካፍ ሱፐር ካፕ ዋንጫ ቲፒ ማዜምቤን በመርታት ባለ ድል መሆንም ችለዋል፡፡

በውጤት የተንበሸበሸ አመትን ላሳለፈውን ሰንዳውንስ በዓለም ክለቦች ዋንጫ ያሳየው ደካማ አቋም እንዲሁም በ2017 ቻምፒየንስ ሊግ ይሁን በፕሪምየር ሶከር ሊግ ያሳየው አቋም የሚዋዥቅ ነው፡፡ ዳግም የደቡብ አፍሪካ ቻምፒዮን ለመሆን የነበረውን ሰፊ እድልም በሚጥላቸው ነጥቦች ዝቅ አድርጓል፡፡ አሁን ላይ ከመሪው ቤድቬስት ዊትስ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት ላይ ቢገኘም የአሰልጣኝ ፒትሶ ሞሴሜኔ ቡድን ከዚህ በተሻለ የሊግ ደረጃ ላይ መገኘት እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይሁንና ያለፈውን ሁለት አመት ያለማቋረጥ በሊግ ይሁን በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚገኘው ቡድኑ አሁንም ተፎካካሪ ሆኖ መዝለቁ አስገራሚ ነው፡፡ ለሁለት ተከታታይ አመታት ብራዚሎቹ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ለማድረግ የጊዜ እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡ በአለም ክለቦች ዋንጫ መሳተፋቸውም የነበራቸውን የሊግ ጨዋታዎች እንዲራዘሙ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ባለፉት ወራት ላይ የጨዋታ መደራረብ በቡድኑ ላይ እንዲከሰት አድርጓል፡፡ ከዚህ ችግር ጋር እየታገለም ቢሆን የሞሴሜኔ ስብስብ አሁን ላይ ወደ ተሻለ አቋም እየተመለሰ ይገኛል፡፡

የ2016/17 የሊግ ጉዞ

በ2016/17 የሰንዳውንስ የሊግ ጉዞ ክለቡ ካደረጋቸው 28 ጨዋታዎች 16 ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታዎች ተረቷል፡፡ በሰባት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥቷል፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ በ55 ነጥብ ከመሪው ቤድቬስት ዊትስ በሁለት ነጥብ ብቻ አንሶ ሁለተኛ ነው፡፡ ረቡዕ ባደረጉት የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ ላለመውረድ ከሚታገለው ባሮካ ጋር 2 አቻ የተለያዩት ብራዚሎቹ በውድድር ዓመቱ 48 የሊግ ግቦች በማስቆጠር ከ15ቱ ክለቦች የተሻሉ ሲሆን የተቆጠረባቸው የግብ መጠንም (16) ትንሹ ነው፡፡ የዚምባቡዌው ኢንተርናሽናል አማካይ ካማ ቢሊያት በስምንት የሊግ ግቦች የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን ወደ ብቃቱ እየተመለሰ መሆኑን ፍንጭ እያሳየ የሚገኘው ፐርሲ ታኦ ሰባት ግቦች ማስቆጠር ችሏል፡፡ ቴምባ ዝዌኔም በተመሳሳይ 7 ግቦች ማስቆጠር ችሏል፡፡

እድል የተቀላቀለበት የ2016 ቻምፒየንስ ሊግ ስኬት

የ2016 ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ለመሆን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ረጅም ጉዞ አስፈልጎታል፡፡ ብዙዎች ሰንዳውንስ ለቻምፒየንስ ሊግ ድል የበቃበት መንገድን ከእድል ጋር ያያይዙታል፡፡ ሰንዳውንስ በምድብ ጨዋታዎች፣ በግማሽ ፍፃሜ እና በፍፃሜ ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎቹ የተሻለ የጨዋታ አቀራረብን እና ብልጫን ወስዶ ማሸነፉ ግልፅ ነው፡፡ ወደ ምድብ ለመግባት ግን የኤኤስ ቪታ ክለብ ቅጣት አስፈላጊ ነበር፡፡

ሰንዳውንስ ወደ ምድብ ለመግባት የተፋጠጠው ከዲ.ሪ. ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብ ጋር ነበር፡፡ በውጤቱም የኪንሻሳው ክለብ ወደ ምድብ ማለፍ የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ወደ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የወረደው ሰንዳውንስ በዚህኛም ውድድር ድል አልቀናውም ፤ በጋና ሚዲአማ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ እምብዛም ለአፍሪካ ውድድሮች ትኩረት እንደማይሰጡ የሚነገርላቸው የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ፈለግን የተከተለ የሚመስለው ሰንዳውንስ ዳግም ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ የተመለሰው በአስገራሚ ግጥምጥሞሽ ነው፡፡ ቪታ ክለብ በሰንዳወንሱ ጨዋታ ያልተገባ ተጫዋቾች ማሰለፉን ተከትሎ ከምድብ ሲሰናበት በምትኩ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ተተካ፡፡ ሰንዳውንስ በምድብ ለ ከግብፅ ዛማሌክ፣ ከአልጄሪያው ሲኤስ ሴቲፍ እና ከናይጄሪያው ኢኒየምባ ኢንተርናሽናል ጋር ነበር የተደለደለው፡፡ ሶስቱም ክለቦች ከዚህ ቀደም የቻምፒየን ሊጉን ዋንጫ አንስተው ማወቃቸው እንዲሁም ያላቸው ሰፊ ልምድ ሰንዳውንስ ከምድቡ የማለፍ ተስፋው እንዲቀንስ አድጎታል፡፡ ቢሆንም በሜዳ ላይ የታየው ግን ፍፁም ተቃራኒው ነበር፡፡ ሰንዳውንስ ለተቃራኒ ቡድኖች ፈተና ሆኖ ነበር የቻምፒየንስ ሊግ ጉዞውን የጀመረው፡፡ የማይበገረው ሰቲፍን ወደ አልጄሪያ ተጉዞ 2-0 መምራት ችሏል (ጨዋታው በሴቲፍ ደጋፊዎች ረብሻ ተቋርጧል፤ ይህንን ተከትሎ ካፍ ሴቲፍን ከውድድር ሰርዟል፡፡) በቀሪዎቹ ጨዋታዎችም ዛማሌክን በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ ሲረታ ኢኒየምባን ፕሪቶሪያ ላይ አሸንፎ በመልሱ ጨዋታ 3-1 ተረቷል፡፡ በግማሽ ፍፃሜ እና በፍፃሜ ያገኛቸውን ዜስኮ ዩናይትድ እና ዛማሌክን (በፍፃሜው 3-1) ማሸነፍ ችሏል፡፡

2017 ቻምፒየንስ ሊግ

የዘንድሮ ዓመት ቻምፒየንስ ሊግ የውድድር ቅርፅ ለውጥ በማድረጉ በካፍ የክለቦች ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክለቦች ወደ ምድብ ለመግባት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ጨዋታ ሁለት ብቻ ነው፡፡ ሰንዳውንስም ሁለት ጨዋታዎች በማድረግ ነው ምድብ ማለፍ የቻለው፡፡ የዩጋንዳው ኬሲሲኤን አሳማኝ ባልሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ 3-2 በማሸነፍ ወደ ምድብ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ከፍተኛ የሆነ ጫና ኬሲሲኤ ላይ ማሳየት የቻሉት ብራዚሎቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አከታትለው ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች መምራት ችለው ነበር፡፡ የዩጋንዳው ክለብ በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠራት ወሳኝ ግብ የመልሱ ጨዋታ እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ በመልሱ ጨዋታ ካምፓላ ላይ ባለሜዳዎች የተሻለ ቢንቀሳቀስም ሰፊ ልምድ ያካበተው ሰንዳውንስን ለመጣል ግን በቂ አልነበረም፡፡

የጨዋታ አቀራረብ

በማሜሎዲ ሰንዳውንስ በተለያዩ ቦታዎች በአሰልጣኝነት የሰራው ደቡብ አፍሪካዊው ሱደሽ ሲንግ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ የብራዚሎቹን የጨዋታ አቀራረብ ፣ ወሳኝ ተጫዋቾች ፣ ጠንካራ ጎን እንዲሁም ድክመቶችን እንዲህ ያብራራል፡፡

“ሰንዳውንስ አንድን የጨዋታ ቅርፅ ያለምንም ችግር በቀላሉ መቀየር የሚችል ቡድን ነው፡፡ የተለያዩ የጨዋታ ንድፎች በአንድ ጨዋታ ለመተግበር እንዲችል ሆኖ የተዋቀረ ጥሩ ቡድን ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት ቡድኑ ከኳስ ቁጥጥር ወደ መልሶ ማጥቃት የሚያደርጋቸው የጨዋታ እቅድ ለውጦች በተደጋጋሚ ማየት ይቻላል፡፡ ይህም አምና በቻምፒየንስ ሊግ ስኬታማ አድርጓቸዋል፡፡ የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ የተትረፈረፈው የተጫዋቾች የግል ክህሎት ነው፡፡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በብሄራዊ ቡድ ደረጃ የሚጫወቱ መሆናቸውም ይበልጥ ጠንካራ ቡድን ያደርገዋል፡፡ ዴኒስ ኦኒያንጎ በአሁን ወቅት በአፍሪካ አለ የተባለ ቁጥር 1 ግብ ጠባቂ ነው፡፡ ከዴኒስ ፊት ብራዚላዊው የመስመር ተከላካይ ሪካርዶ ናሺሜንቴ ይገኛል፡፡ ናሺሜንቴ በቴክኒክ ብቃቱ ላቅ ያለ መሆኑ ፣ ጨዋታዎች የሚረዳበት መንገድ እና ጥሩ የፍፁም ቅጣት ምት መቺ መሆኑ ሰንዳውንስ ጠቅሟል፡፡ የመስመር ተከላካዮች ማጥቃትን መሰረት ያደረገ ጨዋታን ይከተላሉ፡፡ ላንገርማን፣ ሞሬና እና ንኮንጋ ወደ ፊት በመሄድ በመስመር በኩል ማጥቃቱን ያግዛሉ፡፡ የቡድኑ አምበል ሆሎምፖ ኬካና ለተከላካዮቹ ሽፋን ከመስጠትም ባለፈ በረጅሙ ወደ ፊት የሚልካቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ለሰንዳውንስ ውጤታማነት ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ በዚህ ላይ ከረጅም ርቀት ግብ ማስቆጥር የተካነ ነው፡፡ የአጥቂ አማካዮቹ ከሌሎቹ ተጫዋቾች ይልቅ ለሰንዳውንስ ቁልፍ ናቸው፡፡ ቢሊያት፣ ዝዌኔ እና ላፎር በጥቂቱ ለመጥራት ወሳኝ ናቸው፡፡ በአጥቂ መስመር ላይ ታኦ ጥሩ ነው፡፡ ቡድኑ ውስጥ እንደድክመት የሚወሰደው ነገር ቢኖር ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የመጋለጥ እድሉ በጣም የሰፋ ነው፡፡ የመስመር ተከላካዮቹ ወደፊት ገፍተው መጫወታቸው በመስመር ላይ ተጋጣሚ ቡድኖች የመልሶ ማጥቃት እድልን በሚያገኙበት ወቅት ሰፊ ክፍት እና የመቀባበያ አማራጮችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ሌላኛው የመሃል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ፍጥነት ይጎድላቸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ለመልሶ ማጥቃት ሲጋለጡ ቡድኑ ኳስን በፍጥነት የማስመለስ ችግር ይታይበታል፡፡ የቅርብ ግዜ አቋማቸው ግራ አጋቢ ቢሆንም አሁን ላይ ወደ ጥሩ ቅንጅት ቡድኑ እየመጣ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ይህ ቡድን ያለፉትን 2 ዓመታት በውድድር ላይ ያለማቋረጥ የተገኘ ቢሆንም በሜዳው ግን ለማሸነፍ የሚያስቸገር ቡድን መሆኑን ነው፡፡”

ቅዱስ ጊዮርጊስ

የቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዘመን ጉዞ ጉራማይሌ መልክ የያዘ ሆኗል፡፡ ፈረሰኞቹ በሀገር ውስጥ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ቢቃረቡም በክለቡ የቅርብ አመታት ታሪክ ደካማ የተባለውን ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በቻምፒየንስ ሊጉ ደግሞ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፈው ምንም ግብ ሳያስተናግዱ በምርጥ አቋም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የምድብ ድልድሉን ተቀላቅለዋል፡፡

የ2009 የሊግ ጉዞ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በደጋፊዎች ተቃውሞ በታጀበ ደካማ አጀማመር የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ቢጀምርም በወሳኝ ጨዋታዎች በሚሰበስባቸው ነጥቦች ታግዞ 3 ጨዋታዎች ብቻ የሚቀሩትን ሊግ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ደደቢትን በ4 ነጥቦች ልዩነት በማስከተል የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቧል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊጉ መሪነት በተጨማሪ በርካታ ጎል በማስቆጠር እና ጥቂት ጎሎች በማስተናገድ በሊጉ ቀዳሚ ነው፡፡ አጥቂው ሳላዲን ሰኢድ ደግሞ እንደ ቻምፒየንስ ሊጉ ሁሉ በፕሪምየር ሊጉ 14 ጎሎች በማስቆጠር የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ነው፡፡

የ2016 ቻምፒየንስ ሊግ ጉዞ

ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና በቻምፒየንስ ሊጉ የመጀመርያ ዙር በቲፒ ማዜምቤ በድምር ውጤት ተሸንፎ ነበር ከመንገድ የቀረው፡፡ በቅድመ ማጣርያው የሲሸልሱ ሴንት ሚሼልን አዲስ አበባ ላይ 3-0 ሲያሸንፍ በመልሱ ቪክቶርያ ላይ 1-1 ተለያይቶ ወደ 1ኛው ዙር ማለፍ ችሏል፡፡ የወቅቱ የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ቲፒ ማዜምቤን በመጀመርያ ጨዋታ ባህርዳር ላይ ከመልካም እንቅስቃሴ ጋር 2-2 አቻ ተለያይቶ በመልሱ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፎ በድምር 2-3 ውጤት ወደ ተከታዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል፡፡

2017 ቻምፒየንስ ሊግ

ፈረሰኞቹ የዘንድሮውን ቻምፒዮንስ ሊግ የጀመሩት ወደ ሲሸልስ በማቅናት በቅድመ ማጣርያው ኮት ዲኦርን 2-0 በመርታት ነበር፡፡ በመልሱ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ 3-0 በማሸነፍ በድምር 5-0 ውጤት የመጀመርያውን ዙር መቀላቀል ችለዋል፡፡

በአንደኛው ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስ ኮንጎ ሪፐብሊኩ ኤሲ ሊዮፓርድስ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒው የመጀመርያውን ጨዋታ 1-0 አሸንፎ ከዶሊሴ ተመልሷል፡፡ በመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከአስደናቂ የደጋፊ ድባብ ጋር ታጅቦ 2-0 በመርታት በድምር 3-0 አሸናፊነት የምድብ ድልድሉን ተቀላቅሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጠቃላይ በዘንድሮው የማጣርያ ጉዞ በ4 ጨዋታ 8 ጎሎች ሲያስቆጥር ምንም ግብ አላስተናገደም፡፡ አጥቂው ሳላዲን ሰኢድም 5 ጎሎችን በ4 ጨዋታዎች ማስቆጠር ችሏል፡፡

የጨዋታ አቀራረብ ፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎን

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባት የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ሳምንታት በሀገር ውስጥ ሊግ ጥሩ አቋሙን እያሳየ ነው። በዚህም ተከታታይ አራት ጨዋታዎችን በድል ሲያጠናቅቅ በመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም ። ምንም እንኳን ውድድሮቹ የተለያዩ ቢሆኑም የክለቡ ወቅታዊ የሊግ መልካም አቋም የተጨዋቾቹን የዕዕምሮ ጥንካሬ ከፍ የሚያደርገው ይሆናል። በተለይም ግብ በቀላሉ የማይስተናገድበት የቡድኑ የኋላ መስመር ከሜዳ ውጪ ለሚደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ትልቅ የቤት ስራ ይጠበቅበታል። የአስቻለው ታመነ እና የሳላዲን ባርጌቾ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ከሮበርት ኦዶንካራ ልምድ ጋር ተዳምሮ ለጊዮርጊስ ጥንካሬ ዋነኛ መሰረት ነው። የማጥቃት ተሳትፏቸው እምብዛም የሆኑት የመስመር ተከላካዮችም የተጋጣሚን የመስመር እንቅስቃሴ ለመግታት የተሻለ እምነት የሚጣልባቸው ናቸው። ሁል ጊዜም ጥያቄ የሚነሳበት የቡድኑ የመሀል ክፍል ግን አሁንም በጥርጣሬ የሚታይ አይነት ነው። አብዛኞቹን ጨዋታዎች በተከላካይ አማካይነት ቦታ ላይ ተሰልፎ እየተጫወተ የሚገኘው ናትናኤል ዘለቀ በቦታው ላይ ብቁ ነው ማለት ቢቻልም ከፊት ለፊቱ ባለው ቦታ ላይ ተጨዋቾች እየተቀያየሩ መጫወታቸው የአማካይ መስመሩን አሳስቶታል። በዚህ ቦታ ላይ በተሻለ ብዙ ጨዋታዎችን ይሰለፍ የነበረው ምንተስኖት አዳነ በቅጣት አለመኖሩ ክፍተቱን የሚያጎላው ቢሆንም በቅርብ ጨዋታዎች ላይ በመስመር አጥቂነት እያገለገለ የሚገኘው አብዱልከሪም ኒኪማ ለአጥቂ አማካይነት የተሰራ ተጨዋች ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም የአጥቂው ሳላዲን ሰይድን አለመኖር ተከትሎ አዳነ ግርማ በፊት አጥቂነት ላይ ሊሰለፍ የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ ኒኪማ ሁነኛ አጣማሪ እንዳያጣ ያሰጋል። ክለቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይዞ ከሄደው ስብስብ ውስጥ ቦታውን ለመሸፈን ምንያህል ተሾመ የተሻለ አማራጭ ቢሆንም ተጨዋቹ ከረጅም ጊዜ ጉዳት መመለሱ ሁኔታውን ሊያከብደው ይችላል። የክለቡ የመሀል ሜዳ ደካማ ጎኑ አሁን ላይ በቅጣት ካጣቸው ተጨዋቾቹ ጋር ተዳምሮ በጨዋታው የመሀል ሜዳ የበላይነት እንዳይወሰድበት የሚያሰጋ ነው። ሆኖም በመስመር አጥቂነት ቦታ ላይ ሊሰለፉ ይችላሉ ተብሎ ከሚጠበቁት አቡበከር ሳኒ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ የተሻለ ሽፋን ለአማካይ መስመሩ በመስጠት ወይንም የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ይህንን የቡድኑን ደካማ ጎን ለማሻሻል የሚቻልበት አማራጭ አለ። ከዚህ በተጨማሪም ከአብዱልከሪም ኒኪማ ጀርባ ናትናኤል እና ተስፋዬን በማሰለፍ ባለክህሎቶቹ የሰንዳውንስ አማካዮችን እንቅስቃሴ የማጨናገፍ እቅድ አሰልጣኙ ይዘው ሊገቡ ይችላሉ፡፡ አምና ከቲፒ ማዜምቤ ጋር ባደረጉት ጨዋታም ሁለቱን የተከላካይ አማካዮች አጣምረው መልካም እንቅስቃሴ ማሳየት ችለው ነበር፡፡

ከዚህ ውጪ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ ድልድሉ ውስጥ የገባበት መንገድ አሁንም ለተጨዋቾቹ የራስ መተማመን ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። በተለይም በሊዮፓርድስ የደርሶ መልስ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሾች ቡድኑ ውጤቱን ለማስጠበቅ የተጠቀመበት እንደቡድን የመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን የመፍጠር ሂደት በዚህኛውም ጨዋታ ላይ መተግበር ከቻለ ውጤት ይዞ የመመለስ ዕድሉ በእጁ ነው።

ፈረሰኞቹ ከሁሉም በላይ ሶስት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት እና ቅጣት ማጣታቸው የቡድኑ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ የሜዳውን አብዛኛው ክፍል በታታሪነት የሚሸፍነው ምንተስኖት አዳነ ፣ ባለፉት ተከታታይ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ድንቅ የነበረው በኃይሉ አሰፋ እና ግብ አስቆጣሪው ሳላዲን አለመኖር ክፍተት መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ሳላዲን ከ2010 ጀምሮ በተለያዩ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች እና በብሄራዊ ቡድን ያካበተው ልምድ የቡድኑን ደረጃ ጨምሮት የነበረ እንደመሆኑ አለመኖሩ ክፍተት ይፈጥራል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (4-2-3-1)

ዴኒስ ኦንያንጎ

ታፔለሎ ሞሬና – ላንገርማን- ታቦ ንታቴ – ሪካርዶ ናሺሚንቶ

ሎምፎ ኬካና – ላኪ ሞሆሚ

አንቶኒ ላፎር – ካማ ቢልያት – ያኒክ ዛክሪ

ፔርሲ ታው

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

ፍሬዘር ካሳ – አስቻለው ታመነ – ሳላዲን በርጊቾ – አበባው ቡታቆ

ናትናኤል ዘለቀ – ተስፋዬ አለባቸው – አብዱልከሪም ኒኪማ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አዳነ ግርማ – አቡበከር ሳኒ

Leave a Reply