የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ የዲ.ሪ. ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብን ቱኒዝ ላይ አስተናግዶ ከኃላ ተነስቶ 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በስታደ ኦሎምፒክ ደ ራድስ በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የእንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ የበላይነት ይዘው ግጥሚያውን ጨርሰዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው እና በ8ኛው ደቂቃ በአማካዩ ፋክረዲን ቤን የሱፍ እና ሰአድ ባጉር አማካኝነት ያገኛቸው እድሎች በኤስፔራንስ በኩል ሳይጠቀሙባቸው ቀርቷል፡፡ በ10ኛው ደቂቃ የኪንሻሳው ሃያል ክለብ ቪታ በካሜሮናዊው ያዚድ አቶባ አማካኝነት መሪ መሆን የቻለበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ በቻን 2016 ድንቅ ብቃቱን ለሃገሩ ያሳየው አቶባ በመልሶ ማጥቃት ሩዋንዳዊው ኢንተርናሽናል እርነስት ሱጌራ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ክልሉ ይዞ በመግባት በግብ ጠባቂው ሞይዝ ቤን ሻሪፋ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ቢሆንም ኤስፔራንስ አቻ ለመሆን አስር ደቂቃዎች ብቻ በቂ ነበሩ፡፡ ከፍተኛ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ኤስፔራንሶች በኮትዲቯራዊው ፎሲኒ ኩሊባሊ በግንባሩ በመግጨት የአቻነቷን ግብ አስገኝቷል፡፡ ኩሊባሊ በጨዋታው ላይ የተሰለፈ ብቸኛው ቱኒዚያዊ ያልሆነ ተጫዋች ሲሆን በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ የገቡ እና በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ የክለቡ ተጫዋቾች በሙሉ ቱኒዚያዊያን ናቸው፡፡
ኤስፔራንስ ከአምስት ደቂቃዎች በኃላ መሪነቱን መጨበጥ ችሏል፡፡ በውድድር አመቱ በጥሩ መልኩ ለክለቡ ግልጋሎትን እየሰጠ የሚገኘው ጠሃ ያሲን ኬኔሲ በፍፁም ቅጣት ምት የቱኒዙን ክለብ መሪ አድርጓል፡፡ ከእረፍት መልስም የኤስፔራንስ ጫና የቀጠለ ሲሆን በ51ኛው ደቂቃ የቪታው ሊቶምቦ ባንጋላ በሁለት ቢጫ ከሜዳ መወገዱ ይበልጥ ቡድኑን ጎድቶታል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ኢሃብ ሙባረኪ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አኒስ ባድሪ ከመረብ አዋህዶ ልዩነቱን ወደ 2 አስፍቷል፡፡ ኤስፔራንስ ከነበረው ብልጫ አንፃር በሰፊ ግብ ልዩነት ጨዋታውን ማሸነፍ ይችል ነበር፡፡
በ2016 ከሌላኛው የቱኒዚያ ሃያል ክለብ ኤቷል ደ ሳህል ተለያይተው ኤስፔራንስን የያዙት አንጋፋው ቱኒዚያዊው አሰልጣኝ ፋውዚ ቤንዛርቲ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን በድል ከፍተዋል፡፡ በአንፃሩ የቪታ ኮንጎዋዊው አሰልጣኝ ፍሎሮ ኤቤንጌ ቡድናቸው በማጥቃቱ በኩል ከፍተኛ ድክመት ያለበት ጨዋታ መሆኑን ሳያስረዳቸው አይቀርም፡፡