ቅዱስ ጊዮርጊስ በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ምድብ ድልድል የገባ ሲሆን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የሚገጥሙበት የቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ ይደረጋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሃገር ውስጥ የሊግ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ክለቡ የሊጉ አናት ላይ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው መቀመጡን ተከትሎ ዋንጫ የማሸነፍ ተስፋው የሰፋ ሆኗል፡፡ የፈረሰኞቹ ሆላንዳዊው ዋና አሰልጣኝ ማርቲነስ ኤግናቲየስ (ማርት ኖይ) ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች በቻምፒየስ ሊግ እንደሚጠቅማቸው ተማምነዋል፡፡ “ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ከተመለከትን በአሸናፊነት ነው የተወጣነው፡፡ ሶስቱን ከአዲስ አበባ ውጪ ያገኘናቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ በወልዲያ፣ ጅማ እና ድሬዳዋ ያደረግናቸው ጨዋታዎች አስቸጋሪዎች ነበሩ፡፡ በየጨዋታዎቹ በጥሩ መልኩ የተደራጀ አጨዋወትን ነው ቡድናችን የተከተለው፡፡” ብለዋል፡፡
በምደብ ሐ ከሚገኙ ክለቦች በምድብ ተሳትፎ አድርጎ የማያውቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው፡፡ አሰልጣኝ ኖይም የምድብ ጨዋታዎች ቀላል እንዳልሆኑ አስረድተዋል፡፡ “የመጨረሻዎቹ 16 ከተቀላቀልክ በኃላ ቀላል ጨዋታ የሚባል የለም፡፡ ቀላል ክለብ ወይም ደካማ ተጋጣሚ የምትለው አይኖርም፡፡ ተጋጣሚዎች ሁሌም በዚህ ውድድር ጠንካራ ናቸው፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው፡፡ ምክንያም እኛ ስንሳተፍ ይህ የመጀመሪያችን ነው፡፡ አሁን ላይ ወደ ቱኒዝ፣ ኪንሻሳ እና ፕሪቶሪያ ሄደን እንጫወታለን፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የአፍሪካ ቻምፒዮን ናቸው፡፡ ስለዚህም ለእነሱ ፈተና ለመሆን ተዘጋጅተን ነው የሄድነው፡፡”
የቻምፒየንስ ሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሳላዲን ሰዒድ እና አማካዩ ምንተስኖት አዳነ በቅጣት ከቡድኑ ውጪ ናቸው፡፡ የመስመር ተጫዋቹ በኃይሉ አሰፋም ከጉዳት ቢያገግምም ለጨዋታው ብቁ አለመሆኑን ተከትሎ ከቡድኑ ጋር አልተጓዘም፡፡ ሆኖም ይህንን ተከትሎ በቡድኑ ላይ ስለሚኖሩ ለውጦች ኖይ ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ ” 18 ለጨዋታው ብቁ የሆኑ ተጫዋቾች አሉን፡፡ ሳላ እና ምንተስኖት በቅጣት ምክንያት ለጨዋታው አይደርሱም ስለዚህም በቀጣይ ለምናደርገው ጨዋታ ዝግጅት አዲስ አበባ ላይ ሆነው ይሰራሉ፡፡”
ኖይ አሁንም የረጅም ግዜ የቻምፒየንስ ሊግ እቅዳቸውን ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ “አሁን ላይ ለሰንዳውንስ የተዘጋጀነው ታክቲክ አለ፡፡ በመቀጠል የሊግ ጨዋታ አለብን ከዛ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ እዚህ እንገጥማለን ስለዚህ ጨዋታዎችን ቀስበቀስ ነው መመልከት የምፈልገው፡፡ ሁሉም ስድስት ጨዋታዎች ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቸጋሪ ነው የሚሆኑት፡፡ ተስፋ አለኝ ተጫዋቾቻችን ለጨዋታዎቹ ብቁ እንደሚሆኑ፡፡”
በአፍሪካ 16 አመት በላይ የሰሩት የቀድሞ የሞዛምቢክ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞ ኖይ በቡርኪናፋሶ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን እና በታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ቆይታ ማድረጋቸው በአህጉር ውድድሮች ላይ ልምድ እንድይዙ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡