“ስለጨዋታው ከዴኒስ ጋር ለረጅም ጊዜያት ተነጋግረናል” ሮበርት ኦዶንካራ

በ2017 ካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ በምድብ ሐ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሪቶሪያ በሚገኘው በሉካስ ማስተርፒስስ ሞርፒ ስታዲየም የአምናው የውድድሩ ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ቅዳሜ ምሽት ይገጥማል፡፡ በ1997 እንደ አዲስ ቻምፒየንስ ሊግ በሚል መዋቅር ውድድሩ ከተጀመረ ወዲህ አንድም የኢትዮጵያ ክለብ ምድብ ውስጥ ገብቷ የማያውቅ ሲሆን ፈረሰኞቹ ወደ 16 የሰፋው የምድብ ድልድል በአዲሱ መዋቅር ማለፍ ችለዋል፡፡

ዩጋንዳዊው የክለቡ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ስለማሜሎዲ ሰንዳውንስ፣ ቻምፒየንስ ሊጉ ጨዋታ እና የብሄራዊ ቡድን አጋሩን ዴኒስ ኦኒያንጎ በተቃራኒ ስለመግጠም እና ሌሎች ሃሳቦችን ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርቷል፡፡

ስለጨዋታው

“እኔ በግል የሰንዳውንስ የጨዋታ እንቅስቃሴ ስከታተል ቆይቻለው፡፡ ከቋሚ በረኛው እስከተቀያሪ ተጫዋቾቹ በሙሉ ጠንቅቄ አውቃቸዋለው፡፡ የተወሰኑ የእኛ ልጆች ላያውቋቸው ይችላሉ ቢሆንም እየመከርናቸው ነው፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች ጭንቀት እና ስሜታዊነት ሊፈጠርባቸው ይችላል፡፡ ትልቅ ተጫዋቾች መሆንን ማስመስከር ከፈለክ ግዴታ በእንደዚህ አይነት ትልቅ ጨዋታዎች መታየት አለብህ፡፡ እኛም ለጨዋታው ተዘጋጅተናል፡፡ ጥሩ ጨዋታ ለማሳየት ነው ፍላጎታችን፡፡ መቶ በመቶ መድረስ የሚገባኝ የጨዋታ ፊትነት ላይ አልገኝም ነገርግን ግዴታ ተሰልፌ የቡድናችንን በራስ መተማመን ማሳደግ ስላለብኝ ለጨዋታው ተዘጋጅቻለው፡፡”

ለቅዱስ ጊዮርጊስ በምድቡ የተሰጠው ግምት

“ለእኛ የተሰጠው ግምት አነስተኛ መሆኑ አይጎዳንም ይጠቅመናል እንጂ፡፡ ተጋጣሚዎቻችን ስለእኛ በደንብ አያውቁም፡፡ ምንአልባት እኔ እና ሳላዲንን ነው ሊያውቁ የሚችሉት፡፡ ቀሪዎቹን ተጫዋቾቻችን የማወቅ እድላቸው የጠበበ ነው፡፡ የአጨዋወት ስትራቴጂያቸውን ሲያወጡ እኔ ላይ እንዴት ግብ ማስቆጠር እንዳለባቸው እና ሳለዲንን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ነው የሚሆነው፡፡ ሳላዲን በእርግጥ ወደ ፕሪቶሪያ አልተጓዘም፡፡ ፈተና የሚሆነው የእኔን ድክመት እና ጥንካሬ ዴኒስ ለቡድን አጋሮቹ ማሳወቁ ነው፡፡”

ዴኒስ ኦኒያንጎን በተቃራኒ ስለመግጠም

“አዎ የምድብ ድልድሉ ይፋ ከሆነበት ግዜ አንስቶ ስለጨዋታው ከዴኒስ ጋር ለረጅም ግዜያት ተነጋግረናል፡፡ ሁለታችንም ደስተኞች ነን በመገናኘታችን፡፡ ሁሉም ከብሄራዊ ቡድን አጋር ጋር ስትገናኝ ደስተኛ ትሆናለህ፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ይህ የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉም ጨዋታ ልክ እንደፍፃሜ ጨዋታ ነው፡፡ ሁለታችንም ለክለቦቻችን ነጥብ ለማስገኘት ነው ሜዳ የምንገባው፡፡ ሰንዳውንስ ትልቅ ክለብ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ፈተና የበዛበት ጨዋታ ነው የሚሆነው ምክንያቱም እኛ የምድብ ጨዋታ ልምድ የለንም እንዲሁም በጥራት ደረጃ ከሰንዳውንስ እናንሳለን፡፡ ቢሆንም ልንፈራቸው አይገባም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ላይ ነጥብ ለማግኘት ነው አላማችን፡፡”

በቻምፒየንስ ሊግ ግብ ስላልተቆጠረበት የተከላካይ መስመሩ

“አራት ጨዋታዎች ላይ ግብ አልተቆጠረብንም፡፡ እኔም በጥሩ ብቃት ላይ ሆኘዬ ቡድኔን እያገለገልኩ እገኛለው፡፡ በተለይ ከሊዮፓርድስ ጋር ኮንጎ በተጫወትንበት ወቅት ጥሩ ተጫውተናል፡፡ ሁሉም ለተከላካዮቻችን እኔ ስኖር በራስ መተማመናቸው ከፍ ይላል፡፡ እነዛ ጨዋታዎች አልፈዋል አሁን ላይ የምንገጥመው ሰንዳውንስ ነው፡፡ አስቸጋሪ ጨዋታ እንደሚሆን እናምናለን ግን የጠበቀ እና የተደረጃ ሁነን ለጨዋታው ቀርብን ውጤት ይዘን ለቀሪዎቹ ጨዋታዎች ማሰብ ነው የምንፈልገው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *