የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ነገ ይጠናቀቃል

በአብርሀም ገ/ማርያም እና ቴዎድሮስ ታከለ


የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን በነገው እለት በሚደረግ የፍጻሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል፡፡ የምድብ ሀ አሸናፊው ሀዋሳ ከተማ የአምና ክብሩን ለማስጠበቅ ከምድብ ለ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም 08:00 ላይ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡

8 ክለቦች በተወዳደሩበት ምድብ ሀ በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መሻሻል ያሳየው ሀዋሳ ከተማ ከተከታዩ ንግድ ባንክ በ4 ነጥብ ርቆ በ31 ነጥቦች የምድቡ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡ በተክለብርሀን አምባዬ እና ሲዳማ ቡና ከውድድሩ መውጣት ምክንያት በ7 ክለቦች መካከል የተካሄደው እና እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ አሸናፊው ባልተለየበት ምድብ ለ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን በ1 ነጥብ በመብለጥ በ25 ነጥቦች በበላይነት አጠናቋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ደግሞ ምድባቸውን በ2ኝነት ያጠናቀቁ ክለቦች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የእድሜ ተገቢነት ምርመራ ከሌላው ጊዜ በተሻለ በማከናወኑ በአንጻራዊነት በእድሜ ተገቢ የሆኑ ተጫዋቾች የተካፈሉበት ውድድር ነበር፡፡ በዚህም ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር እንዲካሄድበት አስችሏል፡፡

አምና የውድድሩ አመዛኝ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታድየም እንደመካሄዳቸው የተመልካች እና የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት ማግኘት የቻለ ሲሆን የማጠቃለያ ውድድሩም ለተጫዋቾች የበለጠ የመጫወት እድል በመስጠት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በዘንድሮው ውድድር ጨዋቻዎቹ በተለያዩ ሜዳዎች መደረጋቸው እና የማጠቃለያ ውድድር አለመኖሩ ከአምናው ያነሰ ትኩረት እንዲሰጠው ያስገደደ ሆኗል፡፡


የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ብርሀኑ ወርቁ (ሀዋሳ ከተማ)

የፎርማት ለውጥ እና በርካታ ጨዋታ ማድረግ

የዘንድሮው ውድድር ከሌላው ጊዜ የተሻለ ነው፡፡ ብዙ ጨዋታዎች ካለፈው አመት በዚህ አመት ተደርገዋል፡፡ በተደጋጋሚ ማድረጋቸውም ለእድገታቸውም ወሳኝ ነው ከአምናው ፎርማቱ መቀየሩ የተሻለ ነው፡፡

የማጠቃለያ ውድድር መቅረት

ከዚህ በፊት የማጠቃለያ ውድድር ነበረው፡፡ እኔ በጊዜው ባልኖርም አሁን ባለው የውድድር አካሄድ ለሁሉም ክለቦች አመቺና ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በደርሶ መልሶ የሚደረግ ጨዋታ ነው፡፡ የአምናው በጥቂት ጨዋታ የተገደበ ውድድር በመሆኑ አቅምህን ለማየት በጣም አሰቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን የተሻለ ነው በየከተማው ተዟዙረህ ሰለምትጫወት የዚህ አመት ጉዞ የተሻለ ነው፡፡

የሀዋሳ ከተማ በተከታታይ ለፍጻሜ መቅረብ

እውነት ለመናገር አዲስ ቡድን ነው የሰራሁት፡፡ እኔም ለስራው አዲስ ነኝ ፣ አዳዲስ ተጫዋቾችም ናቸው የተካተቱበት፡፡ እንደአዲስነታቸው ጥሩ ነገር አላቸው ስንጀምር 14 ቀን ብቻ የዝግጅት ጊዜ ነበረን፡፡ አሁን ግን ባሉን ክፍትና የዕረፍት ጊዜያት ችግሮቻችንን ቀርፈን ለዚህ ፍፃሜ ቀርበናል፡፡ ጥሩ ስለሆንን የአምናውን ክብር ዳግም እናገኘዋለን የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

የተጫዋቾቹ ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ተነሳሽነት

ሀዋሳ ከተማ አላማው ታዳጊዎችን ሁሌም ማፍራት ነው፡፡ ከ12 ፣ 14 እና 15 እንዲሁም 17 እና 20 አመት በታች ቡድን አለው፡፡ እኚህ ሁሉ ወደ ዋናው ቡድን ለማደግ ስለሚያስቡ ውጤታማ ለመሆን ይተጋሉ፡፡ አሁን ከእኔ ጋር ያሉ ተጫዋቾች ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ያላቸው ህልም እያየሁ ነው፡፡ እርግጠኛም ነኝ ያሳኩታል፡፡


አሰልጣኝ ደረጄ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በምድብ ለ የነበረው ፉክክር

ትልቅ ፉክክር የነበረበት ውድድር ነበር፡፡ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ወደ ፍጻሜው የሚያልፈው ቡድን አልተለየም ነበር፡፡ ይህም የነበረውን ፉክክር የሚያሳይ ነው፡፡

ትኩረት መነፈግ

በፌዴሬሽኑ በኩል MRI ላይ ጊዜ ወስዶ በመስራቱ በፕሮግራም እና ከጨዋታ ሜዳ አንጻር ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ይህ ለቀጣይ አመት መታረም ይኖርበታል፡፡ ለተመልካችም ፣ ለሚድያም ፣ ተጫዋቾችን መመልከት ለሚፈልጉ አሰልጣኞችም አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

በምድቡ የነበረው የጨዋታ ብዛት ማነስ

እዚህ እድሜ ላይ ክትትል አለማድረጋችን ነው ችግር የሆነው፡፡ አንድ ተጫዋች ምንም ያህል ጥሩ አቅም ቢኖረው በአመት 10 እና 15 ጨዋታ ብቻ በማድረግ አቅሙን ማጎልበት አይችልም፡፡ ተጫዋቾቻችን ቢያንስ 30 ጨዋታ ማድረግ ካልቻሉ ሌሎች ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ እንቸገራለን፡፡

ከሀዋሳ ከተማ ስለሚጠብቃቸው ፉክክር

ዘንድሮ ቡድኑን የመከታተል እድል አላገኘሁም፡፡ ሆኖም ስለ ቡድኑ ባገኘሁት መረጃ ትልቅ አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ያሰባሰበ እና ምድቡንም በጥሩ ሁኔታ ያጠናቀቀ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቀናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ለዋናው ቡድን ለማደግ ያላቸው ዝግጁነት

የውድድሩ አላማ ከዋንጫ ባለፈ ለዋናው ቡድን ግብአት የሚሆኑ ተጫዋቾችን ማፍራት ነው፡፡ በተጫዋቾች ላይ ለውጥ ካላመጣ ዋንጫ ብቻውን ትርጉም አይኖረውም፡፡ እንደ አሰልጣኝም እንደ ክለብም አላማችን የተጫዋቾችን አቅም ማሻሻል ነው፡፡ በዚህም ተጫዋቾቹ ለውጥ እያመጡ ነው፡፡

Leave a Reply