የ2017 ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ሲካሄዱ በሜዳቸው የተጫወቱት አብዛኞቹ ቡድኖች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ የተጠበቀው የኦምዱሩማን ደርቢ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ብቸኛው ጨዋታ ነው፡፡
ምድብ ሀ
የምድቡ ሁለት ጨዋታዎች ዓርብ ሲደረጉ የከተማ ባላንጣው ኤል ሜሪክን ያስተናገደው አል ሂላል 1-1 ሲለያይ ኤቷል ደ ሳህል አዲስ መጪውን ፎሮቫያሪዮ ደ ቤይራን 5-0 ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ አል ሂላል እና ኤል ሜሪክን ባገናኘው የኦምዱሩማን ደርቢ ጨዋታ ክለቦቹ ሳይሸናነፉ አቻ ወጥተዋል፡፡ በአል ሂላል ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በቱኒዚያዊው ነቢል ኮዎኪ የሚሰለጥኑት ባላሜዳዎቹ በናይጄሪያው ሾዎባሌ አዚዝ የ31ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 መምራት ችለዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ዲያጎ ጋርዚያቶው ሜሪክ ኤል ሳማኒ ሳደልዲን ባስቆጠራት ግሩም ግብ አንድ ነጥብን ማሳካት ችሏል፡፡ ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች መካከል የማሸነፍ ከፍተኛ ትግል እና ጥሩ ፉክክር ማሳየት ችለዋል፡፡
በምድቡ ሌላ ጨዋታ በስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ ኤቷል ደ ሳህል በምድብ ለመጀመሪያ ግዜ እየተሳተፈ የሚገኘውን ፎሮቫያሪዮ ደ ቤይራን ገጥሞ በቀላሉ 5-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ብራዚላዊው አጥቂ ዲዬጎ አኮስታ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ጊኒያዊው አልካሊ ባንጉራ፣ አልጄሪያዊው ሃሚር ቦአዛ እና ሃምዛ ላህማር ያስቆጠሯቸው ግቦች በፈረሳዊው የቀድሞ የዩኤስኤም አልጀር እና ቲፒ ማዜምቤ አሰልጣኝ ሁበርት ቬሉድ የቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ውድድራቸውን በድል እንዲከፍቱ አስችሏል፡፡ ምድቡን ኤቷል ደ ሳህል ሲመራ ኤል ሜሪክ እና አል ሂላል ይከተላሉ፡፡
ምድብ ለ
ዩኤስኤም አልጀር እና ዛማሌክ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የምድብ ውድድራቸውን ሶስት ነጥብ በማሳካት ጀምረዋል፡፡
አልጀርስ በሚገኘው ስታደ ጁላይ 5 1962 በተደረገ ጨዋታ ዩኤስኤም አልጀር አል አሃሊ ትሪፖሊን 3-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ባለሜዳዎቹ በሊቢያው ክለብ ከፍተኛ ጫናን በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ያሳረፉ ሲሆን ሁለት ግዜም የግቡ አግዳሚ እና ቋሚ መልሶባቸዋል፡፡ ፋሩክ ቻፊ በ31ኛው ደቂቃ ሞክታር ቤንሙሳ ያሻገረውን ቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት ዩኤስኤም አልጀርን ቀዳሚ ሲያደርግ ለዕረፍት ከመውጣታቸው በፊት ማዳጋስካራዊው ካርሎስ አንድሪያማሂትሲኖሮ ባስቆጠረው ግብ ልዩነቱ ወደ 2 ሰፍቷል፡፡ መደበኛው የጨዋታው ክፍለግዜ ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃዎች ሲቀሩት ኦሳማ ዳርፋሎ ከካርሎስ የተመቻቸለን ኳስ ተጠቅሞ የማሳረጊያውን ግብ አስገኝቷል፡፡
አሌክሳንደሪያ በሚገኘው ቡርጅ ኤል አረብ ሲታዲየም ዛማሌክ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዞ ካፕስ ዩናይትድን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሺካባላ ከመስመር ያሸገለትን ኳስ በአግባቡ የተጠቀመው ባሰም ሙርሲ ዛማሌክን ቀዳሚ ሲያደርግ ናይጄሪያዊው ስታንሊ ኦዋዉቺ ሁለተኛውን ግብ በ83ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡ ምድቡን ዩኤስኤም አልጀር እና ዛማሌክ በግብ ክፍያ ተበላልጠው መምራት ጀምረዋል፡፡
ምድብ ሐ
በምድቡ ብቸኛ ጨዋታ ኤስፔራንስ ኤኤስ ቪታ ክለብ 3-1 መርታቱ ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃሉ፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም አሌክሳንደሪያ ላይ አል አሃሊ ዛናኮን ያስተናግዳል፡፡
ምድብ መ
በምድቡ አንድ ብቸኛ ጨዋታ ሲደረግ ዋይዳድ ካዛብላንካ የካሜሮኑን ኮተን ስፖርትን 2-0 ረቷል፡፡ በስታደ መሃመድ አምስተኛ በተደረገው ጨዋታ ዋይዳድ በዊሊያም ጄቦር እና አሚን አቱቺ ግቦች ነው ሶስት ነጥብ ማሳካት የቻለው፡፡ ላይቤሪያዊው ጄቦር በሞሮኮ ቦቶላ ሊግ እያሳየ ያለው መልካም እንቅስቃሴ ተከትሎ ከገልፍ ሃገራት ክለቦች ከወዲሁ የዝውውር ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡ ጄቦር የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ በ39ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር በ63ኛው ደቂቃ አቶቺ ከመሃመድ ኦንዣም የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል፡፡
የአርብ ውጤቶች
ኤቷል ደ ሳህል 5-0 ክለብ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ
አል ሂላል 1-1 ኤል ሜሪክ
ዩኤስኤም አልጀር 3-0 አል አሃሊ ትሪፖሊ
ዛማሌክ 2-0 ካፕስ ዩናይትድ
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ 3-1 ኤኤስ ቪታ ክለብ
ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 2-0 ኮተን ስፖርት
የዛሬ ጨዋታዎች
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
አል አህሊ ከ ዛናኮ