ፕሪሚየር ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮንነቱን ለማረጋገጥ ይጫወታል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬ በወራጅ ቀጠናው በሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎች እና ቻምፒዮኑን ቡድን በሚለይ ጨዋታ ይቀጥላል፡፡

በ9 ሰአት ከተከታዩ በ17 ነጥቦች ርቆ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ይርጋለም አቅንቶ የ2006 አም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮንነቱን ለማረጋገጥ ይጫወታል፡፡ ፈረሰኞቹ ይንን ጨዋታ በድል ከተወጡ አልያም አቻ ከወጡ የሊጉን ዋንጫ በታሪክ ለ26ኛ ጊዜ (የኢትዮጵ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ በ1990 ከተጀመረ ወዲህ ለ11ኛ ጊዜ) ማሸነፋቸውን ያረጋግጣሉ፡፡

ሌሎች 3 ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9፡00 በአዲስ አበባ እና በክልል ስታዲየሞች ይካሄዳሉ፡፡ ከሁሉም በተለየ ትኩረት የሳበው ግን በመብራት ኃይል እና ሐረር ሲቲ መካከል ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ 12ኛ እና 13ኛ ላይ የሚገኙት ክለቦች በመሃከላቸው ያለው የነጥብ ልዩነት 3 ብቻ እንደመሆኑ በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት ትንቅንቅ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በ9 ነጥቦች ግርጌ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ለመቆየት ተአምር ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ ወደ ሀዋሳ በሚያደርገው ጉዞ የግድ አሸንፎ ከላይ የሚገኙት ክለቦች የግድ ነጥብ መጣል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናግዳል፡፡ በ7ኛው ሳምንት የወላይታ ድቻን መረብ በጌድዮን አካፑ ግብ ለመጀመርያ ጊዜ ለደፈረው ሙገር እና በሁለተኛው ዙር ተዳክሞ ለቀረበው ወላይታ ድቻ ያን ያህል አስፈላጊ ጨዋታ አይደለም፡፡

በ10 አሰት አበበ ቢቂላ ላይ ኢትዮጵ ቡና አርባምንጭ ከነማን ያስተናግዳል፡፡ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ የመነመነው ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ደረጃውን አስጠብቆ ለመጨረስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

በ11፡30 ሌላው በመውረድ ስጋት ላይ የሚገኘው ዳሽን ቢራ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ይፋለማል፡፡ የመብራት ኃይል እና ሐረር ሲቲ እርስ በእርስ ፍልሚያ ለዳሽን ቢራ መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ይህንን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡

የመከላከያ እና ደደቢት ግጥሚያ ጦሩ በናይል ቤዚን ቻምፒዮንሺፕ እየተሳተፈ በመሆኑ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *