የ2017 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ትላንት ሲጀመሩ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ የአምናውን ሻምፒዮን ማሜሎዲ ሳንዳውንስን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለግብ አቻ ተለያይቷል ።
ከጨዋታው በፊት ጥሎ በነበረው ዝናብ ምክንያት ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ላይ በስቴድየሙ ጥቂት ተመልካች የነበረ ቢሆንም በሂደት ግን የተመልካቹ ቁጥር ተሻሽሎ የታየ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያዊያን ከባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች በላይ በቁጥር ልቀው ታይተዋል ። እስከጨዋታው መገባደድ ድረስም በኢትዮጵያ ባንዲራ ደምቀው የታዩት ደጋፊዎች ለፈረሰኞቹ ሞቅ ያለ ድጋፍ በመስጠት ቡድኑ ላሳካው ነጥብ ትልቅ እገዛ አድርገዋል ።
ሳላዲን ሰይድን እና ምንተስኖት አዳነን በቅጣት በሀይሉ አሰፋን ደግሞ በጉዳት ያጡት ጊዮርጊሶች ራምኬል ሎክን እና ተስፋዬ አለባቸውን ወደ ቋሚ አሰላለፍ በማምጣት አዳነ ግርማን በፊት አጥቂነት ተጠቅመዋል ። ቡድኑ ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ናትናኤል ዘለቀን እና ተስፋዬ አለባቸውን ከአራቱ ተከላካዮች ፊት በማድረግ እንዲሁም ከአዳነ ጀርባ የነበሩትን ፕሪንስ ፣ ኒኪማን እና ራምኬልንም ወደራሱ ሜዳ በማስጠጋት ጥንቃቄን መሰረት ያደረገ አጨዋወትን ተግብሯል ።
ይህ የጊዮርጊስ አጨዋወት ለብራዚሎቹ ፈተና ሆኖባቸውም አምሽቷል ። በተመሳሳይ የ 4 2 3 1 ቅርፅ ጨዋታቸውን የጀመሩት ሳንዳውንሶች ከኋላ ኳስ መስርተው በአጭር ቅብብል ወደተጋጣሚያቸው ሜዳ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ቢታዩም በአብዛኛው የጨዋታ ክፍል ይህ አካሄዳቸው ፍሬያማ አልነበረም ። ይልቁኑም ከመሀል ተከላካዮቹ በድንገት በቀጥተኛ አጨዋወት ለአጥቂዎቹ ይላኩ የነበሩ ኳሶች የተሻለ አደጋ እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል ። ምንም እንኳን በተደጋጋሚ የቦታ መለዋወጥ ያደርጉ በነበሩት ሶስቱ የአጥቂ አማካዮች ቪላካዚ ፣ ላፉር እና ሞዳይስ እንዲሁም በፈጣን የመስመር ተከላካዮቻቸው በኩል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጊዮርጊሶችን ሰብረው ለነግባት ጥርት ቢያደርጉም በመጀመሪያው ግማሽ የፈጠሯቸው አደገኛ ሙከራዎች ሁለት ብቻ ነበሩ ። እነዚህ በፈጣኑ ዚምባቡያዊ አጥቂ ቢሊያት በ5ኛው ደቂቃ እና በጨዋታ አቀጣጣዩ ሞዳይስ በ8ኛው ደቂቃ የተፈጠሩት ዕድሎች በሮበርት ኦዱንካራ አስደናቂ ብቃት ከሸፉ እንጂ ሻምፒዮኖቹን ባለድል የማድረግ አቅም ነበራቸው ።
በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች እነዚህን ከባድ ሙከራዎች ያስተናገደው የፈረሰኞቹ የተከላካይ ክፍል 26ኛው ደቂቃ ላይ ከግዙፉ የመሀል ተከላካይ ሶማሆሮ ለብቸኛው አጥቂ ቢሊያት ተልኮ ሮበርት በፍጥነት ወጥቶ ካዳነበት ኳስ ውጪ ሌላ ዕድል ለተጋጣሚው አልሰጠም ። ሆኖም በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ይሁኑ እንጂ ጊዮርጊሶች ኳሶችን ካስጣሉ በኋላ ለማጥቃት የሚያደርጉት የነበረው ሙከራ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ያልታገዘ እና በተሳሳቱ ቅብብሎች ምክንያት ይቋረጥ የነበረ በመሆኑ ወደ ሳንዳውንሶች የግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገር ታይቷል ። በመጀመሪያው ግማሽም አዳነ ግርማ 34ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ሞክሮ ዴኒስ ኦንያንጎ በቀላሉ ከያዘበት ኳስ ውጪ ሌላ ሙከራ ማስመዝገብ አልቻሉም ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጊዮርጊሶች እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው እምብዛም አይለይም ። በእርግጥ በዚህኛው የጫወታ ክፍለጊዜ ቡድኑ ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኝም በፍጥነት ቦታቸው ላይ በመገኘት ክፍተቶቻቸውን ይሞሉ የነበሩትን የሳንዳውንስ ተጨዋቸችን ለማለፍ ግን አልቻለም ። በተለይም በ51ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስ ከግራ መስመር ያሻማው ኳስ እና በ53ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል በቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ ሲሞክር ተከላካዮች የተደረቡበት አጋጣሚዎች ለዚህ ማስረጃ የሚሆኑ ነበሩ ። ከዚህ ውጪ ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ጊዮርጊሶች ይበልጥ ውጤቱን ለማስጠበቅ በጥልቀት በመከላከል ነበር ጨዋታውን የጨረሱት ። በዚህ ሂደት ውስጥም ያስር ሙገርዋ ፣ ምንያህል ተሾመን እና በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አቡበከር ሳኒን በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና አዳነ ግርማ ቀይረው በማስገባት የቡድኑን የመከላከል አጨዋወት በአዲስ ጉልበት አጠናክረው እስከ ጨዋታው ማብቂያ ድረስ ዘልቀዋል ።
ይህን የመከላከል አጨዋወት ለማለፍ የተቸገሩት ሳንዳውንሶች ከግራ መስመር ከ ላፉር በተነሳ ኳስ 57ኛው ደቂቃ ላይ ንፁህ የማግባት ዕድል ቢፈጥሩም ቪላካዚ ቢሚያስገርም ሁኔታ ከግበ ጥቂት ሜትሮች ላይ ስቶታል ። ሰዐቱ በገፋ ቁጥርም እየተዳከመ በመጣው የአማካይ ክፍላቸው የመጨረሻ ዕድል የመፍጠር ብቃት ደስተኛ ያልሆኑ የሚመስሉት አሰልጣኝ ሞሲማኔ ሁለቱን የአጥቂ አማካዮቻቸውን ላፉርን እና ቪላካዚን በዛክሪ እና ታው ተክተው ማተካከያ ቢያደርጉም ጨዋታውን የሚያሸንፍላቸውን ጎል ግን ማግኘት አልቻሉም ። በርግጥ ቡድኑ ከለውጦቹ በኋላ የተሻለ ጫና ፈጥሮ በመጫወት ብዛት ያላቸው የቆሙ ኳስ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢችልም የሮበርትን መረብ ለመድፈር ግን ሳይችል ቀርቷል ። በመጨረሻም የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ያለግብ ሲጠናቀቅ ክለቦቹ ባሳኩት አንድ ነጥብ ትላንት በሌላኛው የምድቡ ጨዋታ ክለብ ቪታን 3-1 ድል ማድረግ የቻለውን የቱኒዚያውን ኤስፒራንስን በመከተል በምድቡ ላይ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ቦታን መያዝ ችለዋል ። በቀጣይም ማክሰኞ ግንቦት 15 ላይ ማሜሎዲ ሳንዳውንስ ወደ ኪንሻሳ አምርቶ ክለብ ቪታን ሲገጥም በዛው ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ላይ ኤስፒራንስን የሚያስተናግድ ይሆናል ።