ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ ፉስ ራባት፣ ዜስኮ እና ሴፋክሲየን አሸንፈዋል

በቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በሜዳቸው የተጫወቱት ፉስ ራባት፣ ዜስኮ ዩናይትድ እና ሴፋክሲየን ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የምድብ ጨዋታቸውን በድል አስጀምረዋል፡፡ ፉስ ራባት የዩጋንዳውን ኬሲሲኤን 3-0 ሲረታ ሴፋክሲየን ምባባኔ ስዋሎስን ዜስኮ ዩናትድ ስሞሃን በተመሳሳይ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡

በምድብ ሀ የሚገኙትን ፉስ ራባትን እና ኬሲሲኤን ባገናኘው የስታደ ፉስ ራባቱ ጨዋታ የሞሮኮ መዲና ክለብ በቀላሉ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ አምስት ያህል ቋሚ ተሰላፊዎቻቸውን በጉዳት እና ቅጣት ያጡት የካምፓላው ክለብ በጨዋታ በእጅጉ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ ብራሂም ኤል ባህሪ በሰባተኛው ደቂቃ ፉስን ቀዳሚ ሲያደርግ ጋምቢያዊው የሱፋ ኒጂ ልዩነቱን ወደ ሁለት ያሰፋበትን ግብ ለዕረፍት ከማምራታቸውን በፊት አስቆጥሯል፡፡ በ77ኛው ደቂቃ ካሪም ቤንአሪፍ በጥሩ የመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ተጠቅሞ የፉስን መሪነት ወደ ሶስት አስፍቷል፡፡ ምድቡን ከወዲሁ ፉስ ራባት መምራት ጀምሯል፡፡

በምድብ ለ በቱኒዚያው ሴፋክ ከተማ በሚገኘው ስታደ ታይብ ሚሂሪ በተደረገው ጨዋታ ሴፋክሲየን ለመጀመሪያ ግዜ ተሳታፊ የሆነውን የስዋዚላንዱን ምባባኔ ስዋሎስን 1-0 አሸንፏል፡፡ ስዋሎስ ከባለሜዳው ያነሰ የአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ልምድ ያለው በመሆኑ ሴፋክሲየን በሰፊ ግብ እንደሚያሸንፍ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ወጥ አቋም ማሳየት ያልቻለው የ2013ቱ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ የሴፋክሲየንን የድል ግብ አላ ማርዞኪ በ31ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ በቱኒዚያ ሊግ 1 ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የማይገኘው ሴፋክሲየን ከአሰልጣኝ ነስተር ክላውሰን ጋር ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ተለያይቷል፡፡

በምደብ ሐ ብቸኛ ጨዋታ የዛምቢያው ዜስኮ ዩናትድ ንዶላ ነሚገኘው ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም የግብፁን ስሞሃን አስተናግዶ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኬንያዊው ኢንተርናሽናል ጄሲ ጃክሰን ዌሬ በ73ኛ ደቂቃ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል፡፡

ቀሪ አራት የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡

የአርብ ውጤት

ሱፐርስፖርት ዩናይትድ 2-2 ሆሮያ

የቅዳሜ ውጤቶች

ፋት ዩኒየን ስፖርት 3-0 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ

ሴኤፍ ሴፋክሲየን 1-0 ምባባኔ ስዋሎስ

ዜስኮ ዩናይትድ 1-0 ስሞሃ

የእሁድ ጨዋታዎች

ክለብ አፍሪኬን ቱኒዝ ከ ሪቨርስ ዩናይትድ

ፕላቲኒየምስ ስታርስ ከ ሞሊዲያ ክለብ ዲ አልጀር

ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቪ ዱ ሊቦሎ ከ አል ሂላል ኦባያድ

ቲፒ ማዜምቤ ከ ሲኤፍ ሞናና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *