” በጥንቃቄ በመጫወት ያሰብነውን አሳክተናል” ደጉ ደበበ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ፕሪቶርያ አቅንቶ ከአምናው ባለድል ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት ወሳኝ ነጥብ ይዞ ወጥቷል፡፡ የፈረሰኞቹ አምበል ደጉ ደበበ ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ጨዋታው እንዴት ነበር ?

ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን እናውቃለን፡፡ ሰንዳውስ የአምና የአፍሪካ ቻምፕዮን የነበረና በሊጉም ሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ ጠንካራ ፉክክር እንደሚኖር እናስባለን፡፡ ሆኖም ሁላችንም እያንዳዱ ተጨዋች ጋር ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ ፍላጎት ነበር። ጨዋታውንም እንዳያችሁት ከፍተኛ የሆነ አልሸነፍ ባይነት ትግል ነበር ፤  እያንዳንዱ ተጫዋች ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ይፈልጋል። ምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት አንድ ታሪክ ሰርተናል፡፡ አሁን ደግሞ ሩብ ፍፃሜ ውስጥ በመግባት ሁለተኛ ታሪክ ለመስራት ነው የምናስበው።

ከጨዋታው በፊት አቅዳቹ የነበረው ምንድነው? እሱንስ አሳክተናል ትላላቹ ?

ጨዋታውን በጥንቃቄ ተጫውተን አሸንፈን መውጣት እንዳለብን ተነጋግረናል ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ሜዳው ውስጥም በየቦታቸው ይጫወቱ የነበሩት ተጨዋቾች በሙሉ በሚገርም አይነት የቡድን መንፈስ ነበር ሲጫወቱ የነበረው። እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ድረስ ታግለን ቢያንስ ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን የአቻ ውጤቱን አስጠብቀን ወጥተናል።

በስታድየሙ ለተገኙት ደጋፊዎች ምን ማለት ይቻላል?

በጣም ደስ ይል ነበር አዲስ አበባ ያለን ነበር የሚመስለው። ገና ከኤርፖርት ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ነበር የተቀበሉን ። ሆቴልም እየመጡ አብረውን በመሆን አይዟቹ ምን እናግዝ በማለት ይጠይቁን ነበር። ትላንትም እንዳያችሁት በርካታ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም የእነሱ ደጋፊ አልነበሩም ማለት ይቻላል። ደጋፊዎቻችንም ለእኛ ትልቅ አቅም ነው የሆኑን፡፡ እንደ አምበልነቴ በዚህ አጋጣሚ በቡድኔ ስም ከጎናችን በመሆን ላበረታቱን ደጋፊዎች በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለው።

በቀጣይ ጨዋታዎች ምን እንጠብቅ ?

ከዚህ በኋላ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በሜዳችን እና በደጋፊያችን ፊት እንጫወታለን፡፡ ያው ለሁሉም ጨዋታዎች እኩል ግምት ነው የምንሰጠው ከፍፍለን የምናየው ጨዋታ የለም። ለዚህ ቡድን እንዲህ ብለን አንዘጋጅም፡፡ በቀሩት ጨዋታዎች ሁሉ ታሪክ ለመስራት ያለንን አቅም ለመስጠት ዝግጁ ነን ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *