ሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆነ

የኢትዮጵያ 17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረገ የፍጻሜ ጨዋታ ሲጠናቀቅ ሀዋሳ ከተማ ድራማዊ በሆነ መልኩ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምቶች በመርታት ለተከታታይ የውድድር ዘመን የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

የኢትየጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት 08:30 ላይ የተጀመረው የሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ረጃጅም ኳሶች የበዙበት እና የሀዋሳ ከተማ ሀይል የቀላቀለ አጨዋወት የተስተዋለበት ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚ የሆነበትን ግብ ማግኘት የቻለው ገና በ12ኛው ደቂቃ ነበር፡፡ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ብስራት ተሾመ አስቆጥሯል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተለይም የሜዳውን ስፋት በመጠቀም በተሻጋሪ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ከርቀት የሚሞከሩ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንጻሩ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው ሉክ ፓውሊን አማካኝነት የመሀል ሜዳ ብልጫ መውሰድ ችለዋል፡፡

በ41ኛው ደቂቃ በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል የተፈጸመውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሀብታሙ መኮንን መትቶ የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሚካኤል ንጉሴ አድኖበታል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ተጭነው መንቀሳቀስ ቢችሉም ግልጽ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ከርቀት ከሚሞክሯቸውና በግቡ አናት ወደ ውጪ ከሚወጡ ኳሶች በቀር የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግም አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በ63ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ብስራት ተሾመ ሞክሮ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት እንደምንም ያዳነበት ሙከራ የጊዮርጊስን መሪነት አስተማማኝ ሊያደርግ የሚችል ነበር፡፡

የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪው 3 ደቂቃ መገባደጃ ላይ ሀብታሙ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሚካኤል በግሩም ሁኔታ አውጥቶት ከተገኘው የማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ጸጋዬ ዮሀንስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ከሽንፈት ደጃፍ ደርሶ የነበረው ሀዋሳ ከተማን ህይወት ዘርቶበታል፡፡ የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

አሸናፊውን ቡድን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች ሀዋሳ ከተማዎች የመቷቸውን ኳሶች በሙሉ ወደ ግብነት መቀየር ሲችሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች 2 ኳሶችን በማምከን በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ድል አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ 2008 አሸናፊው ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮም ክብሩን ማስጠበቅ ሲችል በ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግን እየመራ ከመሆኑ ጋር ተደማምሮ ሀዋሳ ከተማ በወጣቶች እግርኳስ ላይ ያለውን የበላይነት ያሳየ ሆኗል፡፡

ጠዋት 03:00 ላይ ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አዳማ ከተማ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ 1-1 አጠናቀው በመለያ ምቶች ንግድ ባንክ 4-2 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

በመዝጊያ ስነስርአቱ ለምድቦቹ አሸናፊዎች ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊው ኒያላ ስፖርት ሽልማት ሲሰጥ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀለትን ዋንጫ ከፍ አድርጓል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለዘመናት ይጠቀምበት የነበረውን አሰራር ዘንድሮ በመቀየር የኮከቦችን ሽልማት በመዝጊያው እለት ከመስጠት ይልቅ ከሌሎች ውድድሮች ጋር በአንድ ላይ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚያበረክት ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *