ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | ቲፒ ማዜምቤ እና ሊቦሎ የምድብ ጨዋታቸውን በድል ጀምረዋል

የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ትላንት በተደረጉ አራት ግጥሚያዎች ሲጠናቀቁ ቲፒ ማዜምቤ፣ ሬክሪቲቮ ሊቦሎ እና ክለብ አፍሪኬን ድል ቀንቷቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች ላይ ልክ እንደቻምፒየንስ ሊጉ ሁሉ በኮንፌድሬሽን ዋንጫው ከሜዳው ውጪ ያሸነፈ አንድም ክለብ የለም፡፡

በምድብ ሀ የሚገኘው ክለብ አፍሪኬን ሪቨርስ ዩናይትድን 3-1 በሆነ ውጤት ረቷል፡፡ ቢላል ኢፋ በ23ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ የቱኒዙን ክለብ መሪ ሲያደርግ የቀድሞ የኤስፔራንስ ኮከብ ኦሳማ ዳራጂ በፍፁም ቅጣት ምት ለእረፍት ከመውጣታቸው በፊት አስቆጥሮ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ የናይጄሪያው ሪቨርስ በ53ኛው ደቂቃ ጆን ኦዱሚጉ ከሳጥኑ ውጪ ባስቆጠራት ግብ ወደ ጨዋታ ቢመለስም የዮቪ ጆሴፍ ዶሃጂ በራሱ ላይ በማስቆጠሩ ክለብ አፍሪኬንን ለወሳኝ ሶስት ነጥብ አብቅቷል፡፡ ምድቡን ፉስ ራባት እና ክለብ አፍሪኬን በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመራሉ፡፡

በምድብ ለ የደቡብ አፍሪካው ፕላቲኒየምስ ስታርስ ከመመራት ተነስቶ ከአልጄሪያው ኤምሲ አልጀር ጋር በሮያል ባፎኬንግ ስታዲየም 1-1 ተለያይቷል፡፡ የአልጀርሱ ክለብ በብራሂም ቦድቦዳ የስድስተኛ ደቂቃ ግብ መምራት ቢችልም ካታሌጎ ኩኖ በ43ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ፕላቲኒየም ስታርስን አንድ ነጥብ እንዲያሳካ አስችሏል፡፡ ምድቡን የቱኒዚያው ሴፋክሲየን ይመራል፡፡

ወደ አንጎላዋ ከተማ ካሉሎ የተጓዘው የሱዳኑ አል ሂላል ኦባያድ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ በሬክሬቲቮ ሊቦሎ 1-0 ተሸንፏል፡፡ የሬክሬቲቮ ሊቦሎን የድል ግብ ከእረፍት መልስ በ72ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፈረንሳዊው ማማዱ ዲያዋና 90 ደቂቃው አልቆ በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ምድቡን ሬክሬቲቮ ሊቦሎ እና ዜስኮ ዩናይትድ በጣምራ ይመሩታል፡፡

የወቅቱ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ቲፒ ማዜምቤ የዋንጫ ክብሩን የማስጠበቅ ዘመቻውን ሉቡምባሺ ላይ የጋቦኑን ሞናናን በማሸነፍ በድል ከፍቷል፡፡ 2-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ወደ ክለቡ በውድድር ዓመቱ የተመለሰው የቀድሞ የማዜምቤ ኮከብ ትሬዘር ማፑቱ በ17ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ሲያስቆጥር በሁለተኛው አጋማሽ ዘምቢያዊው ሬንፎርድ ካላና ጋናዊው ሰለሞን አሻንቴ ያሻገረለትን ኳስ በተመሳሳይ በግንባሩ በመግጨት ማዜምቤን ለድል አብቅተዋል፡፡ ምድቡን ቲፒ ማዜምቤ ይመራል፡፡

የአንደኛ ዙር ውጤቶች

ምደብ ሀ

ፋት ዩኒየን ስፖርት 3-0 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ

ክለብ አፍሪኬን ቱኒዝ 3-1 ሪቨርስ ዩናይትድ

ምደብ ለ

ሴኤፍ ሴፋክሲየን 1-0 ምባባኔ ስዋሎስ

ፕላቲኒየምስ ስታርስ 1-1 ሞሊዲያ ክለብ ዲ አልጀር

ምድብ ሐ

ዜስኮ ዩናይትድ 1-0 ስሞሃ

ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ 1-0 አል ሂላል ኦባያድ

ምደብ መ

ሱፐርስፖርት ዩናይትድ 2-2 ሆሮያ

ቲፒ ማዜምቤ 2-0 ሲኤፍ ሞናና

Leave a Reply