የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ሲደረጉ የምድቡ መሪው ወልዋሎ ወደ አሸናፊነት በመመለስ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል፡፡
አዲግራት ላይ አክሱም ከተማን ያስተናገደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ በነበረው መጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ እሁድ ጠዋት ተሸጋገሯል፡፡ በዚህም እሁድ 05፡00 ላይ በተደረገው ጨዋታ ወልዋሎ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ12ኛው ደቂቃ አጥቂው ቴዎድሮስ መንገሻ ብቸኛዋን ጎል በማስቆጠር ወልዋሎ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡
መቐለ ላይ ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው የመቐለ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ በተነሳው ረብሻ ምክንያት ተቋርጧል፡፡ በጨዋታው ላይ ግብ በመጀመርያው አጋማሽ ጎል በማስቆጠር ቅድሚያ የወሰዱት ባህርዳር ከተማዎች ነበሩ፡፡ ከዕረፍት መልስ በ65ኛው ደቂቃ ለመቐለ ከተማ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ተከትሎ የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ቡድኑ የዳኛው ውሳኔ ፍትሀዊ ያልሆነ መሆኑን ገልፃዋል፡፡ የቅሬታ አገላላፅ ተገቢ አይደለም በሚል የባህርዳር ከተማው ቡድን መሪ አቶ ጥበቡ አብተውን ከሜዳ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን ጨዋታውም ለ15 ደቂቃ ተቋርጦ ከተጀመረ በኋላ መቐለዎች የፍፁም ቅጣት ምቱን ወደ ግብነት ቀይረው አቻ ሆነዋል፡፡ ሆኖም በ80ኛው ደቂቃ በድጋሚ በተነሳው ረብሻ የጨዋታው መንፈስ ተቀይሮ ሜዳው በግርግር ተሞልቷል፡፡ በተነሳው ረብሻም በርካታ ደጋፊዎች ጉዳት አስተናግደው ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ተወስደዋል፡፡ በጉዳዩ ዙርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያለው ነገር የሌለ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ሁኔታውን እየተከታተለች ወደእናንተ የምታደርስ ይሆናል፡፡
ወደ ሽረ የተጓዘው አማራ ውሃ ስራ ሽረ እንዳስላሴን 1-0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥቦች ይዞ ተመልሷል፡፡ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎል ባልተስተናገደበት በዚህ ጨዋታ በተጨማሪ ደቂቃዋች እዮብ ወልደ ማርያም አስቆጥሮ አማራ ውሃ ስራን ወደ ድል መርቶታል፡፡
በተመሳሳይ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ፖሊስ ከ አራዳ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ መደበኛ ክፍለ ጊዜ ግብ ሳስተናገድበት ቆይቶ በተጨማሪ ደቂቃዋች ይርጋለም ማሞ ባስቆጠረው ጎል አዲስ አበባ ፖሊስ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማን ከ ኢትዮ ውሃ ስፖርት ያገናኘው መርሀ ግብር በባለሜዳው 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ለቡራዩ ከተማ አብዱልከሪም ከድር በ35 ደቂቃ ቀዳሚዋን ግብ ሲያስቆጥር የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከተማ አጥቂ አቡበክር ደሳለኝ በ82ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል፡፡
ሱሉልታ ላይ ሱሉልታ ከተማ የምድቡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ሱሉልታ ከተማዋች በጥላሁን ጌታቸው ግብ ቀዳሚ ቢሆኑም በ35ኛው ደቂቃ አባዬ ኢሳያስ ለደብረብርሀን የአቻነቱን ጎል አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ የሱሉልታን የአሸናፊነት ጎል እንዳለ ዘውገ በ42ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ጨዋታው በሱልልታ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በሌሎች ጨዋታዋች ኢትዮጵያ መድህን ወሎ ኮምበልቻን አስተናግዶ 1-0 ሲያሸንፍ ሰበታ ከተማ ከለገጣፎ ለገዳዲ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡