ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ – ጅማ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ድል አስመዝግበዋል 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ሲደረጉ በደረጃ ሰንጠረዡ ቀዳሚዎቹን ሁለት ቦታዎች የያዙት ጅማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ሀላባ ላይ በሳምንቱ ጠጠባቂ የምድብ ለ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን ያስተናገደው ሀላባ ከተማ 1-0 ተሸንፏል፡፡ ያለ ዋና አሰልጣኙ አላምረው መስቀሌ መሪነት ወደ ሜዳ የገቡት ሀላባ ከተማዎች በማጥቃት እንቅስቃሴ የበላይነት መውሰድ ችለው ነበር፡፡ በ8ኛው ደቂቃ በዘካርያስ ፍቅሬ ፣ በ12ኛው ደቂቃ በስንታየው መንግስቱ አማካኝነት ያደረጓቸው የጎል ሙከራዎችም ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

የወልቂጤው አሰልጣኝ አዲስ ካሳ አፈግፍገው በመጫወት በመልሶ ማጥቃት እድሎች ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በ38ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ለማጥቃት ከግብ ክልላቸው ርቀው የወጡት የሀላባ ከተማ ተጨዋቾች ስህተትን ተጠቅመው በአክሊሉ ተፈራ ግሩም ጎል ወልቂጤ 1-0 በሆነ መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

ከዕረፍት መልስ ሀላባዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ቢሆንም ውጤቱን መለወጥ ተስኖቸው ጨዋታው በወልቂጤ ከተማ 1-0 አሸነፊነት ተጠናቋል፡፡

መሪው ጅማ ወደ ነቀምት ከተማ ተጉዞ መሪነቱን ያጠናከረበትን 3 ነጥብ ይዞ ተመልሷል፡፡ የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ ግብ ያልነበረ ሲሆን በተጨማሪ ደቂቃዎች ተመስገን ገ/ኪዳን ብቸኛዋን የአሸናፊነት ጎል አስቆጥሮል፡፡

ሆሳዕና ላይ ሀድያ ሆስዕና ነገሌ ቦረናን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በሟሟቂያ ሰአት ላይ አንድ የነገሌ ቦረና ተጫዋች በህመም ምክንያት ራሱን ስቶ በመውደቁ ወደ ሆስፒታል በአፋጣኝ የተወሰደበት ክስተት በሜዳው የተገኘውን ሁሉ ያስደነገጠ ክስተት ነበር፡፡

በ32ኛው ደቂቃ ሔኖክ አርፊጮ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደግብነት ቀይሮ ሆሳዕና መሪ ቢሆንም በ38ኛው ደቂቃ ነገሌ ቦረና በበኃይሉ ወገኔ አማካይነት አቻ መሆን ችሏል፡፡ ከእረፍት መልስ ሔኖክ አርፍንጮ ያሻገረትን ኳስ በግሩም ሆኔታ አብደላ መሀመድ አስቆጥሮ ሀድያ ሆስዕና አሸናፊ መሆን ያቸለበትን ውጤት አስመዝግቦ ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ ችሏል፡፡

ሻሸመኔ ከተማ ድሬዳዋ ፖሊስን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ አበራ አለሙ በ30ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር በ68ኛው ደቂቃ ምትኩ ማመጫ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡

ስልጤ ወራቤን ከደቡብ ፖሊስ ያገናኘው መርሀ ግብር በስልጤ ወራቤ 1-0 ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ስልጤ ወራቤን አሸናፊ የሚያደርገውን ወሳን ጎል ያስቆጠረው አለማየው ሸብሩ ነው፡፡

ካፋ ቡና አርሴ ነገሌን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ 3 ነጥቦችን ሰብስቧል፡፡ የካፋን ብቸኛ ግብ በ75ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ልመንህ ታደሰ ነው፡፡

በሌሎች ጨዋታዋች ጂንካ ላይ ጂንካ ከተማ ከ ዲላ ከተማ አአ ስታድየም ላይ ፌዴራል ፖሊስ ከ ናሽናል ሴሜንት በተመሳሳይ ጨዋታቸውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *