“ለእግርኳስ ተጨዋች ስነ ምግባር አስፈላጊ ነው” ብርቱካን ገብረክርስቶስ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ትላንት ሲጠናቀቅ ደደቢት ለሁለተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡ ለደደቢት ስኬታማነት ከፍተኛውን ሚና ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል በውድድር ዘመኑ ድንቅ አቋማን ያሳየችው ብርቱካን ገብረክርስቶስ ትጠቀሳለች፡፡ ብርቱካን ስለ እግርኳስ ህይወቷ እና የዘንድሮ ድል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

የእግርኳስ ህይወት

እግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት በልጅነቴ ነው ከወንድሞቼ ጋር ሰፈር ውስጥ እጫወት ነበር፡፡ በወቅቱም እምብዛም የሴቶች እግር ኳስ ያልተስፋፋበት ጊዜ ስለነበር ከወንዶች ጋር ነበር የምጫወተው፡፡ ከዛም ለመጋቢት 28 ትምህርት ቤት መጫወት ጀምሬ ከትምህርት ቤቴ ጋር ቻምፒዮን መሆን ቻልኩ። በመቀጠል ለአዲስ ኮከብ በመጫወት ብቆይም በውጤት በዋንጫ ያልታጀበ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። አዲስ ኮከብ የአቅም ችግር ሲያጋጥመው ሁላችንም ተጨዋቾች ወደ ኤግልስ ክለብ ተዛውረን መጫወት ጀመርኩ፡፡ በኋላም 2004 ወደ ደደቢት አምርቼ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ቻልኩ፡፡ ከሁለት አመት የደደቢት ቆይታ በኋላ ወደ ዳሽን ቢራ አምርቼ ለሁለት አመት ተጫወትኩ፡፡  ከአምና ጀምሮ ወደ ደደቢት ተመልሼ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለሁ፡፡ በእግር ኳስ ህይወቴ አሁን ያለሁበት ደረጃ እደርሳለው ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር።

ስለ ሴቶች እግር ኳስ እድገት

ከትላንት ዛሬ ትልቅ ነው ባይባል በሁሉም ነገር ለውጥ አለ። በክለቦች መብዛት ፣ በታዳጊዎች መምጣት ፣ በክፍያው መጠን ፣ ለሴቶች እግር ኳስ በተሰጠው ትኩረትና እንክብካቤ በጣም ለውጥ አለ። የሴቶች እግር ኳስ ሊያሳድጉ የሚችሉ አካዳሚዎች መብዛታቸው ወደ ፊት ለዕድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።

የሴቶች እግርኳስ ስጋቶች

ብዙም የምሰጋው ነገር የለም፡፡ ሆኖም የሴቶችን እግር ኳስ ያቀጭጨዋል ብዬ የማስበው ክለብ ለማፍረስ የሚያስቡ እና ያፈረሱ ክለቦች መኖር እድገቱ ላይ ያስፈራኛል፡፡ ከዛ ውጪ እኔ እድገቱ ይጨምራል ብዬ ነው የማስበው፡፡

አቋም ጠብቆ ረጅም ጊዜ የመጫወቷ ምስጢር

ምስጢሩ ጠንክሮ መስራት ነው እላለው። ልምምዴን በአግባቡ እሰራለው ፤ ከልምምድም በኋላ በግሌ የምሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ስራዬን ከጨረስኩ በኋላ ተገቢ የሆነ እረፍት አደርጋለው፡፡ ይህ ይመስለኛል አቋሜን ጠብቄ ለመጫወት የረዳኝ ብዬ አስባለው።

ስለ ተደናቂ ስነምግባሯ

ከቤተሰቤ የወረስኩት ይመስለኛል፡፡ ቤተሰቦቼ ሰው ቀና ብለው አያዩም፡፡ ያ ይሆናል እንጂ የተለየ ፀባይ የለኝም፡፡ ነገር ግን ለሚያከብሩኝ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ለታዳጊዎች የምታስተላልፈው መልዕክት

ለእነሱ የማስተላልፈው መልክት ልምምዳቸውን በሚገባ እንዲሰሩ፡፡ ከቻሉም ከሚሰጣቸው ልምምድ ውጭ በግላቸው ልምምዶችን እንዲሰሩ እመክራቸዋለሁ፡፡ ከምንም በላይ ለእግርኳስ ተጨዋች አስፈላጊው ነገር ችሎታ ብቻ ሳይሆን ስነ ምግባር ነው። የቱንም ያህል ችሎታ ቢኖርህ ስነ ምግባር ከሌለህ ያንን ነገር ያጎድፍብሀል፡፡ ስለዚህ በስነ ምግባር እንዲታነፁ መልክቴ ነው።

የዘንድሮው የሊግ ድል

የትኛውም ቡድን አመቱን በሙሉ የሚተጋው አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ ነው። እኛም ከጨዋታ ጨዋታ እያሳየን የመጣነው አቅም ዋንጫ እንድናስብ አድርጎናል፡፡ ትላንትም ከጨዋታ ብልጫ ጋር አሸንፈን ቻምፒዮን መሆናችን ይገባናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *