ጫላ ተሺታ እና ሚኪያስ መኮንን ለሙከራ ወደ ቱኒዚያ ያመራሉ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣርያ ላይ ባሳየው እንቅስቃሴ የተማረኩ ወኪሎች ወደ ታዳጊ ተጫዋቾቹ ፊታቸውን ማዞራቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ የዚህ ቡድን አባል የነበሩት የመስመር አጥቂው ጫላ ተሺታ እና አማካዩ ሚኪያስ መኮንን ለ20 ቀናት ሙከራ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር ቱኒዚያ ለሊት 10፡00 ያመራሉ፡፡

የቱኒዚያው ሃያል ክለብ ኤቷል ደ ሳህል ለተጫዋቾቹ የ20 ቀን የሙከራ ጊዜ የሰጠ ሲሆን ሙከራቸውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ከቻሉ በሁለት ዓመት ውል የሶሱን ታዳጊ ቡድን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡ በሁለት ዓመታት ግዜ የሚያሳዩት እድገት መልካም ከሆነ ለዋናው የኤቷል ደ ሳህል ቡድን ለማሳደግ ወይም ለሌሎች የአውሮፓ ሃገር ክለቦች ለመሸጥ ክለቡ በውል ላይ አስፍሯል፡፡ ጫላ እና ሚኪያስ የሙከራ እድሉን ካገኙ ቢቆዩም የማሊ እገዳን ተከትሎ ቀይ ቀበሮዎቹ ልምምድ ሲጀምሩ ጉዟቸውን ሰርዘው ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅለው ነበር፡፡ የማሊ እገዳ ከተነሳ በኃላ ተጫዋቾቹ በይደር ያቆዩትን የሙከራ እድል አሁን ላይ ለመጠቀም አስበዋል፡፡ በህጉም መሰረት የሚኪያስ አባት አቶ መኮንን ከተጫዋቾቹ ጋር ወደ ሶስ ያመራሉ፡፡

የሲዳማ ቡናው ጫላ የእግርኳስ ህይወቱን በትውልድ ከተማው ሻሸመኔ የጀመረ ሲሆን ባህርዳር ላይ በተደረገው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ኦሮሚያ ወክሎ ባሳየው እንቅስቃሴ ወደ ሻሸመኔ ከተማ ለመዛወር በቅቷል፡፡ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ያሳየው አቋምን ተከትሎ በውድድር አመቱ መጀመሪያ ሱሉልታ ከተማን የተቀላቀለ ቢሆንም ከስድስት ወር ቆይታ በኃላ ወደ ሲዳማ ቡና ዝውውሩን ፈፅሟል፡፡ ሚኪያስ በበኩሉ አምና በሐረር ሲቲ የ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እንዲሁም በብሄራዊ ቡድን ባሳየው ጥሩ አቋም ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀል ችሏል፡፡

የሙከራ እድሉ የማይሳካ ከሆነ ተጫዋቾቹ ወደ ክለቦቻቸው የሚመለሱ ይሆናል፡፡

2 Comments

  1. መልካም እድል የሙከራ ግዜያችሁ የተሳካ እንዲሆን ምኞቴ ነው።

Leave a Reply