” የእኔ አለመኖር ቡድኔን ጎድቶታል ብዬ አላስብም ”  ሽታዬ ሲሳይ 

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ደደቢት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-0 በመርታት ለተከታታይ 2ኛ ጊዜ ቻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ላይ በአጥቂ ስፍራ ቦታ ላይ ስማቸውን በጉልህ ማፃፍ ከቻሉት መሀል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ሽታዬ ሲሳይ በጉዳት የፍጻሜውን ጨዋታ ጨምሮ አመዛኙን የውድድር ዘመን ከሜዳ ለመራቅ መገደዷ ንግድ ባንክ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ማሳረፉንም በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

ሽታዬ ቡድኗን እንዳታገለግል ስላገዳት የጉልበት ጉዳት ፣ ቀጣይ እቅዶቿ እና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጠችውን አስተያየት በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

ስለ ጉዳቷ እና በአሁኑ ወቅት ስለምትገኝበት ሁኔታ

ጉዳቱ ያገጠመኝ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር አራተኛ ሳምንት መርሃግብር ከሀዋሳ ከተማ ጋር ከምናደርገው ጨዋታ በፊት ልምምድ እየሰራንበት በነበረ አጋጣሚ ከቡድን አጋሬ ጋር በተፈጠረ መጠነኛ ግጭት ጉልበቴን ልጎዳ የቻልኩት፡፡ በአሁኑ ወቅት በጉልበቴ ላይ የቀዶ ጥገና አድርጌ ህክምናዬን እየተከታተልኩ እገኛለሁ፡፡

የእሷ አለመኖር በቡድኑ ላይ ስለፈጠረው ተጽዕኖ እና ስለቡድናቸው የውድድር ዘመኑ ጉዞ

እንደአጠቃላይ የቡድናችን አቋም ወጣ ገባ የሚል ነበር፡፡ አንዳንዴ ጥሩ እንዳንዴ ደግሞ መጥፎ የነበርንባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በእኔ እይታ ግን እንደአጠቃላይ ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ የእኔ አለመኖር ቡድኑን ይጎዳዋል ብዬ አላስብም ፤ ምክንያቱም አንድ ቡድን የሚገነባው በበርካታ ተጫዋቾች ነው፡፡ ስለዚህም የአንድ ሰው አለመኖር ያን ያህል ቡድንን ይጎዳል ብዬ አላስብም፡፡ በተጨማሪም በቡድናችን ውስጥ ከኔ የተሻለ ጥሩ አቅም እና ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች ስላሉ በእኔ አለመኖር ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት በአግባቡ መሙላት እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡”

ከተመልካች ጋር ቁጭ ብሎ የቡድን አጋሮቿን ጨዋታ መመልከት ያለው ስሜት

ከተመልካች ጋር ቁጭ ብለህ ጓደኞችህ ሲጫወቱ መመልከት በጣም ይከብዳል፡፡ እንደእኔ እይታ በንጽጽር ሜዳ ውስጥ ገብቶ መጫወቱ እጅጉን ይቀላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ ለእኔ ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ከባድ ጉዳት አጋጥሞኝ ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ርቄ ስለማላወቅ እንደተመካች ቁጭ ብሎ ጓደኞቼ ሲጫወቱ መመልከት እጅጉን ፈታኝና አስጨናቂ አጋጣሚ  ሆኖብኝ ነበር፡፡ ሜዳ ውስጥ ገብተህ ስትጫወት አቅምህ በፈቀደ መልኩ የቻልከውን ያህል ለቡድንህ አበርክተህ የተሻለ ነገር ለመፍጠር ትጥራለህ ፤ ነገርግን ፈጣሪ ስላልፈቀደ እንዳንዴ ቁጭ ብለህ መመልከቱ ለበጎ ነው ብለህ ታልፈዋለህ፡፡

ስለ ቀጣይ እቅድ

አሁን ላይ ሆኜ የማስበው ለቀጣይ የውድድር ዘመን ቶሎ አገግሜ በመድረስ በይልጥ ራሴን አሻሽዬ በመቅረብ ቡድናችን ለተከታታይ ሁለት አመታት ያጣውን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ  ክብር ለማስመለስ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በጋራ ጥረት ማድረግ ነው፡፡

በሊጉ በዘንድሮው አመት ስለተመለከተቻት ምርጧ ተጫዋች

እንደአጋጣሚ ሆኖ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን የመመልከቱ እድሉ ባይኖረኝም በተመለከትኩባቸው  አጋጣሚዎች ግን እንደኔ የደደቢቷ አማካይ ሰናይት ቦጋለ እጅግ ምርጥና አዝናኝ እንቅስቃሴን ማሳየት ችላለች፡፡ ስለዚህም የዘንድሮው የውድድር አመት የኮከብ ተጫዋቾችነት ክብር ይገባታል፡፡

Leave a Reply