በፕሪምየር ሊጉ የመቆየት ትንቅንቅ እና የአሰልጣኞች አስተያየት…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ የ3 ጨዋታዎች እድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ለቻምፒዮንነት ከሚደረገው ፉክክር በበለጠ ላለመውረድ እየተደረገ ያለው ፉክክር በርካታ ክለቦችን ያሳተፈ እና ውጥረት የተሞላበት ሆኗል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ካላቸው የነጥብ መቀራረብ አንጻር የመውረድ እና የመቆየት ህልውናቸው በእያንያንዱ ጨዋታ ውጤት ላይ የተወሰኑት ክለቦች አሰልጣኞችን አናግራ የሚከተሉትን ምላሾች አግኝታለች፡፡


ወላይታ ድቻ

ደረጃ – 11ኛ

ነጥብ – 30

ቀሪ ጨዋታዎችከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (በሜዳው) ፣ ከአርባምንጭ ከተማ (ውጪ) ፣ ከደደቢት (በሜዳው

የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አስተያየት 

” ሐሙስ ከንግድ ባንክ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ልክ 2004 ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ከኒያላ ጋር ካደረግነው ጨዋታ ጋር ነው የምናገናኘው፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ሐሙስ ዕለት ነበር ከኒያላ ጋር ተጫውተን ፕሪምየር ሊግ የገባነው። ይህ የዕለቱ መገጣጠም የበለጠ ያነሳሳናል፡፡ ከንግድ ባንክ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ፕሪምየር ለመግባት እንደምንጫወት አስበን ነው የምንገባው፡፡ ጨዋታውንም አሸንፈን በፕሪምየር ሊጉ እንቆያለን። የተለየ ዝግጅት አላደረግንም ፤ ሆኖም በቂ የሆነ ስራ ሰርተናል፡፡ መሟላት ያለባቸውን ነገሮች አሟልተን እና ድክመቶቻችንን አስተካክለን ጠንካራ ነገሮቻችን አስቀጥለን ወላይታ ድቻን በፕሪሚየር ሊጉ እናቆያለን። ሐሙስም በስታድየሙ የተለየ ድባብ እና የተለየ ስሜት ከደጋፊዎቻችን እንጠብቃለን፡፡ ”


ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ደረጃ – 12ኛ

ነጥብ – 29

ቀሪ ጨዋታዎች – ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ከወልድያ (በሜዳው) ፣ ከሀዋሳ ከተማ (ውጪ)

የአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ አስተያየት

” እዚህ ደረጃ እንደርሳለን ብለን አስበን አናውቅም ነበር፡፡ የሜዳ ላይ የቡድኑ እንቅስቃሴ እና ያለበት ደረጃ የሚመጣጠን ነው ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ወደ ምንም አንገፋውም ችግሩ ያለው እኛው ጋር ነው። ቡድናችን ከበረኛ ጀምሮ ኳስን መስረቶ የሚጫወት የጎል እድሎችን መፍጠር የሚችል ነበር፡፡ ሆኖም የተገኙ እድሎችን አለመጠቀምና በቀላሉ ጎሎች የሚቆጠርብን መሆኑ በዚህ መልኩ እዚህ ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ እንግዲህ እዚህ የገባነው እኛው ነን ማውጣትም የምንችለው እኛው ነንና ይህን ታሪካዊ ቡድን ለማዳን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን። ቡድኑም መትረፍ አለበት ብለን ጠንክረን እየሰራንም እንገኛለን፡፡ ”


ጅማ አባ ቡና

ደረጃ – 13ኛ

ነጥብ – 28

ቀሪ ጨዋታዎች – ከወልድያ (ውጪ) ፣ ከሀዋሳ ከተማ (በሜዳው) ፣ ከድሬዳዋ ከተማ (ውጪ)

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አስተያየት

“ለጨዋታዎቹ የተለየ ዝግጅት አላደረግንም፡፡ ሆኖም የፊታችን ሐሙስ ጠንካራ ጨዋታ ይጠብቀናል ፤ ጨዋታውንም ለማሸነፍ በጉዳት ያጣናቸውን ተጨዋቾች ህመማቸው አገግመው ተመልሰውልናል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ መንፈስ እና ተነሳሽነት አለ፡፡ ከአመራሩ ጀምሮ የሚደረገው ድጋፍ ፣ ደጋፊው እና ህዝቡ የሚሰጠን ድጋፍ ጥሩ ነው። ተስፋ አለን ፤ ከወልድያ ጥሩ ነገር ይዘን በመምጣት ጅማ አባቡናን በፕሪምየር ሊጉ እናቆያለን።”


ድሬዳዋ ከተማ

ደረጃ – 14ኛ

ነጥብ – 28

ቀሪ ጨዋታዎች – ከሀዋሳ ከተማ (በሜዳው) ፣ ከፋሲል ከተማ (ውጪ) ፣ ጅማ አባ ቡና (በሜዳው)

የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አስተያየት

” የቀሩት ሶስት ጨዋታዎች የድሬዳዋ ከተማን የፕሪምየር ሊግ የመቆየት ህልውናን ስለሚያረጋግጡ በተለየ ትኩረት የምንጫወታቸው ይሆናል። ከወትሮ የተለየ ዝግጅት አላደረግንም ፤ ያም ቢሆን ሦስቱን ጨዋታዎች በድል ለመወጣት የአዕምሮ ስራ ሰርተናል። በሚገባ ሶስቱንም ጨዋታ አሸንፈን ድሬደዋ ከተማን በኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ የምናቆይ ይሆናል። ተጨዋቾቼ ጋር በቀጣይ ጨዋታዎች ሁሉ በድል ለመወጣት ያለው መነቃቃት መልካም ነው። ”


ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ደረጃ – 15ኛ

ነጥብ – 25

ቀሪ ጨዋታዎችከወላይታ ድቻ (ውጪ) ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ)

የአሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ አስተያየት

“በሊጉ ላይ ለመቆየት በቀጣይ ያሉት ጨዋታዎች ለእኛ ወሳኝ ናቸው። በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ነጥቦችን ይዞ መውጣት ይጠበቅብናል፡፡ እንደዛም ሆኖ የሌሎቹን ቡድኖች ውጤት እንጠብቃለን፡፡ ዞሮዞሮ ተጨዋቾቻችን ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ፤ በጥቃቅን ስህተቶች ነው ነጥብ እየጣልን እየወጣን ያለነው። እነዛን ስህተቶች አስተካክለን የተጨዋቾቻንን የማሸነፍ አዕምሮ አሳድገን ቡድኑን በሊጉ ላይ ለማቆየት ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ በቡድኑ ውስጥም ጥሩ መነሳሳት ይገኛል፡፡ ” 

Leave a Reply