የጨዋታ ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ ከፕሪምየር ሊጉ መውረዱን አረጋገጠ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ከተማን 2-0 መርታት ችሏል፡፡  በውጤቱ መሠረትም በ2009 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ በመጣበት እግር ወደ ከፍተኛ ሊጉ መመለሱን አረጋግጧል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ የአሰልጣኝ ሹም ሽር ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎችም በአሰልጣኝ እድሉ ደረጀ እየተመሩ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን ማድረግ ችለዋል፡፡

በጉዳት እጅጉን የተዳከመው ኢትዮጵያ ቡና በዛሬው ጨዋታ ማስመዝገብ ከሚጠበቅበት 6 የተጠባባቂ ተጫዋቾች 5 ተጫዋቾች ብቻ ነበር ማስመዝገብ የቻለው፡፡ አሰልጣኝ እድሉም በዛሬው ጨዋታ ላይ በ4-1-4-1 ቅርፅ ከዚህ ቀደም ከነበረው የቡድን ስብስብ ላይ መጠነኛ የቅርፅና የአጨዋወት ለውጥ ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህም መሠረት በክለቡ ቀሪ ጨዋታዎች ላይ እንዳይሰለፍ ቅጣት ተላልፎበት የነበረው አህመድ ረሺድ ከሚታወቅበት የግራ መስመር ተከላካይነት ከኤፍሬም ወንድወሰን ጋር በመሀል ተከላካይ ስፍራ ሲጣመር መሀል ሜዳ ላይ አብዱልከሪም ሀሰን ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ መጀመርያ 11 መግባት ችሏል፡፡ ወጣቱ አቡበከር ናስርም እንዲሁ በተመሳሳይ መሰለፍ ችሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በ5 ቢጫ ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ላይ መሰለፍ ያልቻለው የቡድኑን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪውን ሀይሌ እሸቱን በፍቃዱ አለሙ ከተካበት ቅያሪ በስተቀር በተመሳሳይ የቡድን ስብስብ 4-2-3-1 ቅርጽ ወደ ጨዋታው መግባት ችሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ በተረጋጋ መልኩ በትእግስት ኳሶችን ከኃላ መስርተው ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በጥንቃቄ ላይ መሠረት አድርጎ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አዲስአበባ ከተማዎች ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይም በ23ኛው ደቂቃ ላይ ከኢትዮጵያ ቡናዎ የግብ ክልል የቀኝ ጠርዝ በጥቂት ሜትሮች ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ምንያምር ጴጥሮስ በቀጥታ ሞክሮ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡

በዛሬው ጨዋታ በስታድየሙ የተለያዩ ክፍሎች የተቀመጡ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ከሰሞኑ ከክለቡ ጋር በእጅጉ ስሙ እያያዘ የሚገኘው የቀድሞው ድንቅ ተጫዋቻቸው እንዲሁም በ1995 እና 96 የክለቡ አሰልጣኝ የነበረውን ኳሳዬ አራጌ ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ እንዲመጣ ድጋፋቸውን በመስጠት “GK IS THE SOLUTION ኳሳዬ ይመለስ” የሚሉ የተለያዩ ጨርቆችን ይዘው ወደ ስታዲየም በመግባት አስነብበዋል፡፡

በ38ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን ሽግግር ባደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ከሳሙኤል ሳኑሚ የተሻገረለትን ኳስ ወጣቱ አቡበከር ነስሩ ከግብ ክልሉ ጠርዝ ላይ በግሩም ሆኔታ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ እንዲሁም ለራሱ በሊጉ ሁለተኛ የሆነችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ44ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ ሳሙኤል ሳኑሚ በግራ መስመር በኩል አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የአዲስአበባ ተከላካዮችን በማለፍ የቡድኑን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በእረፍት ሰአት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ቤት በሚያመሩበት ወቅት በስታዲየሙ የቀኝ ጥላፎቅ አካባቢ የነበሩት የክለቡ ደጋፊዎች ተቋውሞ ሊያሰሙባቸው ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች አዲስ አበባ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ወደ ጨዋታው ልትመልሳቸው የምትችለውን ግብ ግን ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና በኩል በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ሳሙኤል ሳኑሚ በ61ኛው ደቂቃ ያገኘውን ወርቃማ የግብ ማግባት አጋጣሚ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት ለልስበት በተመሳሳይ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱልከሪም ሀሰን የተላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ አብበከር ነስሩ በግብ ጠባቂው አናት በላይ አሳልፎ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት በደረጄ አለሙ ሊከሽፍ ችሏል፡፡

በ70ኛው ደቂቃ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ሀዋሳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ባጋጠመው የትከሻ ጉዳት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ርቆ የነበረው ኤልያስ ማሞ ተቀይሮ በመግባት ለቡድኑ ዳግም ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡

የጨዋታው መገባጀጃ ደቂቃዎች በሙከራዎች ያልታጀቡ ሆነዋል፡፡ ከነአን ማርክነህ ያሳለፈውን ኳስ ሀሪስን ሄሱ ከሳጥን ውጪ ወጥቶ ለመያዝ ያደረገው ጥረት ሜዳው ጭቃማነት ምክንያት በመንሸራተቱ ከግብ ክልል ውጪ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የቅጣት ምት ሳይጠቀሙበት የቀሩበት ሙከራ ከአአ ከተማ በኩል ሲጠቀስ በ82ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት የሞከረው ኳስ በግቡ አግዳሚ የመለሰበት በቡና በኩል የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዱን ሲያረጋግጥ በአመቱ መጀመርያ በወጣው የውድድር ደንብ መሰረት ከ25 ነጥብ በታች ያስመዘገበ ክለብ ወደ አንደኛ ሊግ እንደሚወርድ መደንገጉ አአ ከተማ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ አስገብቶታል፡፡

Leave a Reply