ፕሪሚየር ሊግ ፡ ዋንጫው ወደ ቤቱ ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቻምፒዮኑ ቡድን በይፋ ሲለይ የወራጆቹም ሁሌታ እየለየለት መጥቷል፡፡

ወደ ይርጋለም ተጉዞ ሲዳማ ቡናን የጎበኘው የ25 ጊዜ የሊግ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ 26ኛውን ዋንጫ ፍፁም ገብረማርያም ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ማንሳቱን አረጋግጧል፡፡ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች ከሁለቱ በቀር በሌሎቹ ድል የቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ጨዋታ እየቀረው የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል፡፡

ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር ትላንት በከፊል የተጠናቀቀ መስሏል፡፡ 9፡00 ላበአዲስ አበባ ስታዲየም ዳሽን ቢራ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 11፡30 ላይ መብራት ኃይል ሐረር ሲቲን ሲያሸንፉ ኢትዮጵያ መድን አቻ መውጣቱ የመድን እና የሐረር የመውረድ ነገር ሚዛን እየደፋ መጥቷል፡፡

በከባድ ዝናብ እና በጥቂት የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የታጀበው የዳሽን ቢራ እና የንግድ ባንክ ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስኪጠናቀቅ ድረስ 0-0 የነበሩ ሲሆን በ92ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ጅላሎ ሻፊ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ዳሽን ቢራን አሸናፊ አድርጎታል፡፡

ቀጥሎ በተካሄደው የመብራት ኃይል እና የሐረር ሲቲ ጨዋታ መብራት ኃይል ምናልባትም ከውድድር አመቱ ድንቅ ከሚሰኙ አቋሞች አንዱ ሊያሰኝ የሚችለውን አቋም አሳይቶ በ4-1 አሸናፊነት አጠናቋል፡፡ ለማይዘሙት ምሰሶዎቹ ተሾመ ኦሼ 2 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ አዲስ ነጋሽ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ፍቅረእየሱስ ተክለ ብርሃን በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ለሐረር ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው አቡበከር ደሳለኝ ነው፡፡

ሀዋሳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ከ ሀዋሳ ከነማ ጋር 1-1 በመለያየት ወደ ብሄራዊ ሊግ የሚያደርገውን ጉዞ ገፍቶበታል፡፡ ለሀዋሳ ወንድሜነህ ዘሪሁን ከመድን ተዘራ መንገሻ ግብ አስቆጥረዋል፡፡

ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ሙገርን በብሩክ ቃልቦሬ ብቸኛ ግብ 1-0 ሲያሸንፍ በከባድ ዝናብ ምክንያት 73ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጦ ዛሬ 4 ሰአት ላይ የቀጠለው የኢትዮጵ ቡና እና አርባምንጭ ከነማ ፍልሚያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው ከመቋረጡ በፊት አርባምንጭ ከነማ በገብረሚካኤል ያቆብ ግብ 1-0 ሲመራ ቢቆይም ዛሬ ባደረጉት ቀሪ ደቂቃ (17 ደቂቃ) ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ተከላካዩ ቶክ ጄምስ ባስቆጠራት ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

መከላከያ በናይል ቤዚን ውድድር ላይ ለመካፈል ወደ ሱዳን በማቅናቱ ከደደቢት ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡

ሊጉን ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ58 ነጥቦች ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና በ19 ነጥቦች ርቆ በ39 ነጥቦች ይከተላል፡፡ መድን በ10 ፣ ሐረር ሲቲ በ16 ነጥቦች የመጨረሻውን ደረጃ ሲይዙ ኡመድ ኡኩሪ በ14 ግቦች የሊጉን የከፍተኛ ግብ አግቢነት ሰንጠረዥ ይመራል፡፡

ያጋሩ