የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት መደረግ ሲጀምሩ አዲስ አበባ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ያረገውን ጨዋታ 2-0 ተሸንፏል፡፡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደገበት አመትም ከሊጉ መሰናበቱን ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት አረጋግጧል፡፡ ለመሆኑ ከአዲስ አበባ ከተማ በፊት ምን ያህል ክለቦች በመጡበት አመት ከሊጉ ተሰናበቱ? እውነታውስ ምንን ያመለክታል? ተከታዩ ፅሁፍ ምላሽ አለው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ ከተጀመረበት 1990 ጀምሮ በ20ዎቹ የውድድር ዘመናት 44 ክለቦች ተሳትፈዋል፡፡ ከነዚህ መካከል 17 ክለቦች ባደጉበት አመት ተመልሰው የወረዱ ሲሆን ከነዚህ መካከል 2 ክለቦች ለሁለተኛ ጊዜ በመጡበት አመት ለመውረድ የተገደዱ ክለቦች ናቸው፡፡
ከሚሌኒየሙ ወዲህ የበዛው ፕሪምየር ሊጉን የመቋቋም ፈተና
ከታች በሰንጠረዡ እንደሚታየው የፕሪምየር ሊጉን አመታት ከሚሌንየሙ በፊት እና በኋላ በሚል ለሁለት ብንከፍላቸው ከሚሌንየሙ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚያድጉ ክለቦች ሊጉን መቋቋም እየከበዳቸው እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ከሚሌንየሙ በፊት ባሉት 10 የውድድር ዘመናት 3 ክለቦች ብቻ በመጡበት አመት ወደ ብሄራዊ ሊግ ሲወርዱ ከሚሌንየሙ ጀምሮ ባሉት 11 የውድድር ዘመናት (የአአ ከተማን ጨምሮ) 14 ክለቦች በ16 አጋጣሚዎች ወደመጡበት ተመልሰዋል፡፡ ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለው ጅማ አባ ቡናም የመውረድ እና የመቆየቱ ጉዳይ በቀጣይ ጨዋታዎች እንደሚወሰን ልብ ይሏል፡፡
ክለብ | የወረደበት አመት | |
1 | ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ | 1993 |
2 | ሐረር ከተማ | 1993 |
3 | ብርሀን እና ሰላም | 1995 |
4 | ፋሲል ከተማ | 2000 |
5 | ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት | 2000 |
6 | አዲስ አበባ ፖሊስ | 2000 |
7 | ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ | 2000 |
8 | ጉና ንግድ | 2000 |
9 | ፊንጫ ስኳር | 2000 |
10 | እህል ንግድ | 2000 |
11 | ፌዴራል ፖሊስ | 2000 |
12 | ሜታ አቦ | 2002 |
13 | ኒያላ | 2003 |
14 | ፊንጫ ስኳር | 2003 |
15 | አየር ኃይል | 2004 |
16 | ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት | 2005 |
17 | ወልድያ | 2007 |
18 | ሀድያ ሆሳዕና | 2008 |
19 | አዲስ አበባ ከተማ | 2009 |
*ማስታወሻ – በ2000 የውድድር ዘመን 25 ክለቦች የተሳተፉ ሲሆን 11 ክለቦች ወርደዋል፡፡ የ2001 ደግሞ 16 ክለቦች ተሳትፈዋል |
ይህ እውነታ በ1990ዎቹ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለሚያድጉ ክለቦች ሁኔታዎች አመቺ እንደነበሩ ያሳያል፡፡ ከ1990-1992 የተሳታፊዎች ቁጥር በ2 ክለቦች እየጨመረ እንዲሄድ በመደረጉ በሰስቱ የውድድር ዘመናት የሚያድጉ ክለቦች 3 የነበሩ ሲሆን በአንጻሩ የሚወርደው አንድ ክለብ ብቻ መሆኑ አዲስ የሚያድጉ ክለቦች የመቆየት እድላቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደ መከላከያ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ባንኮች) እና ወንጂ ስኳር ያሉ ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደጉበት አመት አንድም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ዝንባሌያቸው በሊጉ እንዲቆዩ ረድቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ባደገበት 1991 የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችሎ ነበር፡፡
ከሚሌንየሙ ወዲህ የብሔራዊ ሊግ ተሳታፊዎች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት በዞኖች ተከፋፍሎ እንዲካሄድ መደረጉ አንድ ክለብ በአመቱ ውስጥ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ጥቂት እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በዞኑ ብቻ ተገድቦ ጨዋታ ማድረጉም በቀላል ፈተና ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ የሚረዳ ነበር፡፡ እስከ 2007 ድረስ በዚህ መንገድ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የሚጠብቃቸው ረጃጅም ርቀቶች የመጓዝ እና በርካታ ጨዋታ የማድረግ ፈተናን መቋቋም ሳይችሉ ለመውረድ ተገደዋል፡፡ በብሔራዊ ሊጉ እና በፕሪምየር ሊጉ መካከል የነበረው እጅግ የተራራቀ የፋይናንስ ልዩነትን መቋቋም ያልቻሉ ክለቦችም እስከ መፍረስ ደርሰዋል፡፡
የከፍተኛ ሊጉ መጀመር
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሊግ እርከኑ ላይ መካተት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመጡ ክለቦች ጠንክረው እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል፡፡ አንድ የከፍተኛ ሊግ ክለብ እና የፕሪምየር ሊግ ክለብ በውድድር ዘመኑ ተመጣጣኝ ጨዋታ የሚያደርግ ሲሆን ወደተለያዩ ከብሔራዊ ሊጉ በተሻለ ረጃጅም ርቀቶች በመጓዝ የሚጫወቱ በመሆናቸው በሁሉ ረገድ ለፕሪምየር ሊጉ ተዘጋጅተው እንዲመጡ ረድቷቸዋል፡፡በ2000 በመጣበት አመት የወረደው ፋሲል ከተማ እና በ2007 በሊጉ ታሪክ ከታዩ ደካማ ቡድኖች አንዱን ይዞ የቀረበው ወልድያ ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድገው በሰንጠረዡ ወገብ ተደላድለው መቀመጥ መቻላቸውም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ቢወርድም በ20 አመታት የሊጉ ጉዞ ከወረዱ ክለቦች የተሻለ እግርኳስ የሚጫወት እና በቀላሉ የማይሸነፍ ቡድን እንደነበር በርካቶች ይስማሙበታል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በደደቢት 3-0 ከመሸነፉ እና በሁለት አጋጣሚዎች በ2 የግብ ልዩነቶች ከመረታቱ በቀር በውድድር ዘመኑ የተሸነፈባቸው ጨዋታዎች በአንድ የግብ ልዩነት ብቻ ነበሩ፡፡ በአጠቃላ ዘንድሮ ባደጉት ክለቦች ላይ የታየው የብቃት ደረጃ በቀጣዩ አመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ለሚፎካከሩ ክለቦች መልካም መነሳሻ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡