ካሜሩን 2019፡ ካፍ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚዳኙ ዳኞችን ስም ይፋ አድርጓል

ካሜሩን ከሁለት አመት በኋላ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታዎች ከሰኔ ወር ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ፡፡ በ12 ምድቦች ተከፍሎ በሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ኩማሲ ላይ ከጋና ጋር ታደርጋለች፡፡

እሁድ ሰኔ 4 ኩማሲ በሚገኘው ባባ ያራ ስታዲየም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 12፡30 በሚደረገው የጥቋቁር ከዋክብቶቹ እና ዋሊያዎቹን የምድብ 6 ጨዋታ እንዲመሩ ካፍ ሴኔጋላዊያን አርቢትሮችን መርጧል፡፡ የመሃል ዳኛ ማጉቴ ንዳዬ ፣ ረዳቶቻቸው አቡባካር ሲኔ እና ሰርጅ ሼክ ቱሬ ጨዋታው የሚመሩ ይሆናል፡፡ በአራተኛ ዳኛነት ዳዉዳ ጉዬ ከሴኔጋል ሁነዋል፡፡ የጨዋታው ታዛቢ ደግሞ ኬንያዊው መሃመድ ኦማር የሱፉ ናቸው፡፡ በምድቡ ሌላኛው ጨዋታ ሴራሊዮን ኬንያን ቅዳሜ ሰኔ 3 ፍሪታውን በሚገኘው ሲያካ ስቲቨንስ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

በማጣርያው ኢትዮጵያዊያን ዳኞችም ጨዋታዎቹን እንዲመሩ በካፍ ተመርጠዋል፡፡ በምድብ ሁለት ያውንዴ ላይ አዘጋጇ ካሜሩን ከሞሮኮ የሚያደርጉትን ጨዋታ የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ረዳቶቹ ተመስገን ሳሙኤል እና ሃይለራጉኤል ወልዳይ ይመራሉ፡፡ አራተኛ ዳኛ ዘካሪያስ ግርማ ነው፡፡

በተያያዘ ማክሰኞ ለሚደረገው የቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝን ለሚያስተናግድበት ጨዋታ ቦትዋናዊያን ዳኞች ካፍ መርጧል፡፡

Leave a Reply