የጨዋታ ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ለአራተኛ ተከታታይ አመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊነታቸውን አረጋገጡ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን መርሃግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳነ ግርማ ጎል ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 በማሸነፍ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክብርን ለአራተኛ ተከታታይ አመት ማንሳቱን በማረጋገጥ አዲስ ታሪክ መፃፍ ችሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ4-3-3 አሰላለፍ ባሳለፍነው ቅዳሜ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ ከወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ ጋር አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ በቅጣት ያልተሰለፉት ሰልሀዲን ሰኢድ እና ምንተስኖት አዳነን በዛሬው የቡድን ስብስብ ውስጥ ሲያካተቱ ፍሬዘር ካሳና እና መሀሪ መናም ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የተመለሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በአንጻሩ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ቡድን ውስጥ በዛሬው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ መሰለፍ ያልቻለውን የቡድኑን አምበል አዲስ ነጋሽን በአሸናፊ ሽብሩ ብቻ በመተካት በተመሳሳይ የ4-1-3-2 ቅርፅ ጨዋታውን ጀምሯል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከተጋጣሚያቸው እጅጉን ተሽለው ታይተዋል፡፡ በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል በቁጥር በዛ በማለት በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ግብ ለመድረስም ጥረት አድርገዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እጅግ ተዳክመው በታዩበት በዚሁ ጨዋታ በጨዋታው በግሉ በከፍተኛ ብርታት እና ትግት ሲጫወት የነበረው አብዱልከሪም ኒኪማ በግሉ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለመፍጠር ከሚያደርገው ጥረት በስተቀር ቡድኑ እንደ ቡድን እጅግ ተዳክሞ ተስተውሏል፡፡

በ20ኛው ደቂቃ ላይ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ኤሌክትሪክን ከተቀላቀለ በኃላ ጥሩ የሚባልን ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ተክሉ ተስፋዬ ባጋጠመው የትከሻ ጉዳት በብሩክ አየለ ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል፡፡ በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ የተገደበ ቢሆንም ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ኤሌክትሪኮች በ37ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገ/ማሪያም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ፊት ያገኘውን ሰፊ ክፍተት በመጠቀም ኳሱን ከገፋ በኃላ በቀጥታ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡ ቋሚን ለትሞ ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ካደረጓቸው ሙከራዎች የምታስቆጭ ነበረች፡፡

በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ41ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ያገኙትን ኳስ በኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውስጥ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ራምኬል ሎክ ንቁ ሆኖ በቶሎ ውሳኔ መወሰን ባለመቻሉ መክናለች፡፡ እጅግ የተቀዛቀዘ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ አጋማሽ እንቅስቃሴ አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳይታይበት ያለ ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል አድልቶ ቢካሄድም ኤሌክትሪኮች በርከት ያሉ ኳሶችን በመሀል ሜዳ ላይ ከመቀባበል ባለፈ ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም፡፡

በዚሁ አጋጣሚ በኤሌክትሪክ በኩል ተጠቃሽ ከነበሩት የግብ ሙከራዎች መሀል በ48ኛው ደቂቃ ላይ አወት ገብረሚካኤል በተከላካዮች መሀል አሾልክ በሀይሉ ተሻገርን ከሮበርት ኦዶንካራ ጋር 1ለ1 ቢያገናኘውም በሀይሉ ኳሷን ከሮበርት አናት በላይ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ሞክሮ ሮበርት በቀላሉ የያዘበት ኳስ የጨዋታውን መንፈስ መለወጥ የምትችል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ፈጠን ባለ የመስመር አጨዋወት ከሁለቱ መስመሮች በተደጋጋሚ ወደ ኤሌክትሪክ ሳጥን ውስጥ መጣል ቢችሉም ኳሷቹን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም በተለይም አዳነ ግርማ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ያመከነው ግልፅ የግንባር ኳስ የሚጠቀስ ነው፡፡

ጨዋታው በኤሌክትሪኮች የበላይነት እየቀጠለ በነበረበት ሂደት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን የማእዘን ምት ከፍተኛ በሆነ የደጋፊዎቻቸው ድጋፍ ታግዘው አብዱልከሪም ኒኪማ ያሻማውን ኳስ አዳነ ግርማ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ፈረሰኞቹ እጅግ ደማቅ በነበረው የደጋፊዎቻቸው ድጋፍ በመታገዝ ጨዋታውን ተቆጣጥረው በርካታ ለማምከን የሚከብዱ ኳሶችን በማምከናቸው ውጤቱ ሊጠብ ቻለ እንጂ ጨዋታው ከዚህም በላይ በሰፋ የግብ ልዩነት ሊጠናቀቅ በቻለ ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል ሰልሀዲን ሰኢድ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም አዳነ ግርማ በአንድ አጋጣሚ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኙትን ወርቃማ አጋጣሚዎች በአስገራሚ ሁኔታ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡

ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ሶስት ጨዋታዎች እየቀራቸው የተከታዮቻቸው ነጥብ መጣልን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሚል እንደ አዲስ ውድድሩ መካሄድ ከጀመረበት 1990 ጀምሮ 14ኛ የሆነውን የሊግ ዋንጫ እንዲሁም ለተከታታይ አራተኛ አመት ማንንም ጣልቃ ሳይሰገቡ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ታሪክ መስራት ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ኤሌክትሪክ በተከታታይ አመታት እንደነበረው ሁሉ ዘንድሮም የመውረድ ስጋት አንዣቦበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *