የጨዋታ ሪፖርት | ወልድያ ለከርሞ በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ ተቃርቧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት 7 ጨዋታዎች ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ሲደረጉ በወልድያው ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስታዲየም ወልድያ እና ጅማ አባ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጨዋታው በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ የሚገኘው ወልድያ የቀጣይ አመት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥበትን ውጤት ለማስመዝገብ ፣ ባለመውረድ ትንቅንቁ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ጅማ አባ ቡና ደግሞ በሊጉ ለማቆየት ለሚያደርገው ትግል ወሳኝ 3 ነጥቦችን የማግኘት ዕቅድ ይዘው ያደረጉት ጨዋታ እንደመሆኑ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር።

ከጨዋታው መጀመር በፊት በዚህ የውድድር ዘመን ለወልድያ ምርጥ አቋሙን እያሳየ ለሚገኘው ካሜሮናዊው ግብ ጠባቂ ኤሚክሪል ቢሌንጌ በስታድየሙ የተገኘው ተመልካች ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎችም ባነር አሰርተው በስታድየሙ ይዘው በመገኘት ለተጫዋቹ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ፈጣን እና ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ታይቶበታል። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራም በወልድያ በኩል ሃብታሙ ሸዋለም ከቅጣት ምት የላከውን ኳስ ዮሀንስ ሀይሉ በጥሩ ሁኔታ ገጭቶ የጅማ አባ ቡናው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው የያዘበት ነበር። በ12ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ጫላ ድሪባ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ከተጠጋ በኋላ የመታውን ኳስ ጀማል ሲያድንበት በ23ኛው ደቂቃ ወልድያዎች በማራኪ አጨዋወት ወደ ጅማ የግብ ክልል ገብተው በሳጥኑ ውስጥ ውስጥ ያሬድ ብርሀኑ በቄንጠኛ ሁኔታ ያመቻቸለትን ኳስ ጫላ ሞክሮት ጀማል የያዘበት ሌላ በወልድያ በኩል የተደረገ ሙከራ ነበር።

ጅማዎች በተደጋጋሚ በመስመር በኩል በተለይም በአሜ መሐመድ አማካኝነት ወደ ወልድያ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ያን ያህል ስኬታማ አልነበሩም። በ34ኛው ደቂቃ ዮሐንስ ሀይሉ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ጅማ አባ ቡናዎች ወርቃማ የግብ ዕድል ቢያገኙም ሙከራውን ኤሚክሪል ቢሌንጌ በሚገርም ብቃት ሲያከሽፍ የተተፋውን ኳስ ጅማዎች በድጋሚ ሞክረው የወልድያ ተካላካዮች ደርሰው ኳሱን ለማዳን ችለዋል። በ36 ደቂቃ የጅማ አባ ቡና ተጫዋቾች በአሜ መሐመድ ላይ ጥፋት ተሰርቷል ብለው በተዘናጉበት ሰአት ሙሉጌታ ረጋሳ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር። በ41ኛው ደቂቃ ቢሌንጌ በሳጥኑ ውስጥ ተጫዋች ለማታለል ሲሞክር አሜ ኳሱን አግኝቶ ሲሞክር አዳሙ መሐመድ ደርሶ ያዳነበት እና በ45ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ አሜ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ ቢሊንጌ በጥሩ ሁኔታ ያዳነበት ኳሶች በጅማ አባ ቡና በኩል የሚጠቀሱ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ መልኩ የወልድያ የኳስ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራዎች የበላይነት ተስተውሎበታል። ወልድያዎች ያሬድ ሀሰን እና በድሩ ኑርሁሴንን በማስገባት ስኬታማ ሊባሉ የሚችሉ የተጫዋች ቅያሬዎችን ሲያደርጉ በ55ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው በድሩ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ግብ ሞክሮ ጀማል ያዳነበት አደገኛ ሙከራ ነበር። ወልድያዎች ተጭነው መጫወት የቀጠሉ ሲሆን በ60ኛው ደቂቃም ያሬድ ሀሰን ኳሱን እየገፋ ወደ ጅማ የግብ ክልል ከተጠጋ በኋላ ከሳጥን ውጭ ወደግብ ሞክሮ ጀማል ጣሰው ይዞበታል። ከ 5 ደቂቃዎች በኋላም በሁለተኛው አጋማሽ ገብቶ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው በድሩ ኑርሁሴን ሶስት ተጫዋቾችን አልፎ የላከለትን ኳስ ጫላ ከመሞከሩ በፊት የጅማ ተከላካዮች ሲያጥሉት የተመለሰውን ኳስ ምንያህል አግኝቶ ወደ አክርሮ በመምታት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሏል።

ጅማ አባ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ከርቀት ወደግብ በሚመቱ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ63ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ፣ እንዲሁም በ72ኛው ደቂቃ በቢያድግልኝ ኤልያስ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ የተሞከሩ ዒላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን የወልድያው ግብ ጠባቂ ኤሚክሪል ቢሊንጌ መልሷቸዋል።

የእለቱ ዳኛ በጨዋታው ላይ በሚወስናቸው ውሳኔዎች ምክንያት የተጀመረው የደጋፊ ተቃውሞ አቅጣጫውን ቀይሮ ከጅማ አባ ቡና የአሰልጣኞች ስታፍ ጋር ግጭት ውስጥ የከተታቸው ሲሆን በ85ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች እንዲቆም ሆኗል። የጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ በጀማል ጣሰው እና ከጨዋታው መገባደድ በኋላም በሲሳይ ባንጫ ላይ ደጋፊውን ለፀብ የጋበዙ ድርጊቶችንም ታዝበናል።

በዛሬው ጨዋታ ፌድሬሽኑ የዛሬውን ጨዋታ የመራው ኢንርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በተደጋጋሚ በወልድያ ጨዋታ መመደቡ እና ተደጋጋሚ ጊዜ በወልድያ ደጋፊዎች ቅሬታ ያስነሳ መሆኑ ደጋፊዎች በተቃውሞ ለጥቂት ደቂቃዎች ከሜዳ አንወጣም ብለው የነበረ ቢሆንም በፀጥታ ሀይሎች እና በአንዳንድ ደጋፊዎች የማግባባት ስራ ደጋፊው በመጨረሻም ሜዳውን ለቅቆ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልድያ በ34 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ እንደሚቀጥል ማረጋገጥ ችሏል። ጅማ አባ ቡና በአንፃሩ 29 ነጥብ እና 5 የግብ ዕዳ በመያዝ 14ኛ ደረጃን ይዞ በወራጅ ቀጠናው ለመቀመጥ ተገዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *