ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊነቱን በዛሬው እለት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 በማሸነፍ ሲያረጋግጥ በመጪው ማክሰኞ በቻምፒየንስ ሊጉ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ፈረሰኞቹን የሚገጥመው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ በሰአታት ልዩነት የቱኒዚያ ሊግ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
በዛሬው እለት ከዋነኛ ተቀናቃኙ ኤቷል ደ ሳህል የተፋለመው ኤስፔራንስ ከጨዋታው አቻ ውጤት ማግኘት ቻምፒየንነቱን ለማረጋገጥ በቂው ቢሆንለትም 3-0 በማሸነፍ የቱኒዚያ ቦቶላ ሊግ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
ጋይሌኔ ቻላሊ በ14ኛው ደቂቃ ኤስፔራስን ቀዳሚ ያደረገች ጎል ሲያስቆጥር በ31ኛው ደቂቃ አሊ ማቻኒ ሁለተኛውን አክሏል፡፡ ታሀ ያሲን ኬኒሲ የቀይ እና ወርቃማ ለባሾቹን 3ኛ ጎል ከእረፍት መልስ አክሏል፡፡
በማልያ ቀለማቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚመሳሰለው የኤስፔራንስ እንደ ፈረሰኞቹ ሁሉ በሀገሪቱን ሊግ ስኬታማው ክለብ ነው፡፡ በዛሬው እለት ያረጋገጠውን ድል ጨምሮ 27 የሊግ ክብሮች እና 15 የቱኒዝያ ዋንጫ ያሳካ ሲሆን ሁለት የቻምፒየንስ ሊግ ድሎችን በክለቡ የዋንጫ መደርደርያ ላይ ማስቀመጥ ችሏል፡፡ አሰልጣኝ ፋውዚ ቤርዛቲ የቱኒዝያን ሊግ ለ9ኛ ጊዜ በማሸነፍም በቱኒዚያ እግርኳስ ላይ ደማቅ አሻራ ማስፈር ችለዋል፡፡