የሴቶች ጥሎ ማለፍ |  ደደቢት እና ሀዋሳ ከተማ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲያልፉ ንግድ ባንክ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ሀዋሳ ከተማ እና ደደቢት ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያሻግራቸውን ውጤተት አስመዝግበዋል፡፡

ቀደም ሲል በ5፡00 እንዲካሄድ መርሃግብር ተይዞለት የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ስታድየሙ በአትሌቲክስ ውድድር ምክንያት በመያዙ በ8:30 ላይ ነበር የተካሄደው፡፡ ተመጣጣኝ የሆነና በመሀል ሜዳ ላይ በሚደረጉ የኳስ ቅብብሎች ላይ ባመዘነው የጨዋታ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የማጥቃት ወረዳው ላይ ሲበላሽ ተስተውሏል፡፡

በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች በማራኪ ሁኔታ መስርተው የገቡትን ኳስ አይናለም አሳምነው በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረችው ትርሲት መገርሳ ብታቀብላትም ትርሲት ያገኘችውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳትጠቀምበት ከቀረችው ሙከራ በስተቀር በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎችን አልነበሩም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ብዙሀን እንዳለን ፣ ታሪኳ ትቢሶን እንዲሁም ትእግስት ያደታን በማስወጣት ፅዮን እስጢፋኖስ ፣ እፀገነት ብዙነህ እና ሀብታምነሽ ሲሳይ በአንድ ጊዜ ቀይረው በማስገባት በቡድናቸው አጨዋወት ላይ ለውጥ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ይህም ቅያሬያቸው በመጠኑም ቢሆን ለውጥ አምጥቶ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ችለዋል፡፡ ሆኖም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ድንቅ እንቅስቃሴን እያደረገች በምትገኘው የሀዋሳ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ትእግስት አበራ ጥረት የባንክ የማጥቃት እንቅስቃሴ በጎሎች ሳይታጀብ ቀርቷል፡፡ በ71ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክዋ አጥቂ ብዙነሽ ሲሳይ ከሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ግራ ጠርዝ ላይ በቀጥታ አክራሪ የሞከረችው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወደ ውጪ የወጣችው ኳስም በንግድ ባንኮች በኩል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት ለመገባደድ በተቃረበበት ወቅት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በፍፁም ቅጣት ምት አያያዝ ችሎታ የተሻለ ብቃት ያላትን ዳግማዊት መኮንን በንግስት መአዛ ተክተው ማስገባት ችለዋል፡፡

ሁለቱን ቡድኖች ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ሀዋሳ ከተማዎች 5-4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለዋል፡፡

በሁለተኛው ጨዋታ የተገናኙት የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ ደደቢት እና ጥረት ኮርፖሬት ሲሆኑ ሰማያዊዎቹ በሎዛ አበራ ሐት-ትሪክ በመታገዝ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡

እጅግ አሰልቺ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛመም የሚጠቀስ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሲሆን የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዋ ሎዛ አበራ በፍፁም ቅጣት ምት ፣ በጨዋታ እንዲሁም እጅግ ማራኪ የሆን ኳስ ከሳጥን ውጪ በመምታት በማስቆጠር ሐት-ትሪክ መስራት ችላለች፡፡ በዚህም ውጤት መሠረት ደደቢት ሀዋሳ ከተማን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የተሻገረ ሁለተኛው ክለብ ሆኗል፡፡

ውደድድሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል በ08:30 ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ፤ በ10:30 አዳማ ከተማ ከ ጌዲኦ ዲላ ይገናኛሉ፡፡

Leave a Reply