ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ –  ወልዋሎ ነጥብ ሲጥል ተከታዮቹ ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አርብ ግንቦት 11 በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ሲደረጉ መሪው ወልዋሎ ነጥብ ጥሏል፡፡ ተከታዮቹ መቀለ ከተማ ፣ ሽረ እንዳስላሴ እና ባህርዳር ከተማም ከመሪው ያላቸውን ልዩነት ማጥበብ ችሏል፡፡

ወደ ደብር ብርሃን የተጓዘው የምድቡ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ የምድቡ ግርጌ ሰሜን ሸዋ ደብርብርሃን ጋር ተገናኝቶ ጨዋታውን ያለ ግብ አጠናቋል፡፡

ሱሉልታ በሚገኘው ያያ ሪዞርት ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርትን ከ መቀለ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በመቀለ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ መቀለ ቀዳሚ መሆን የቻለበትን ግብ በአዲስአለም ደሰለኝ አማካኝነት በ35ኛው ደቂቃ ላይ ሲያስቆጥር በ38ኛው ደቂቃ ተመስገን አዳሙ የመቀለን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ በ42ኛው ደቂቃ አስራት ሸገሬ ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርትን ወደ ጨዋታው መመለስ ቢችልም ሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ ጨዋታው በመቀለ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ባህርዳር ላይ ሱልልታ ከተማን ያስተናገደው ባህርዳር ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ወላይታ ድቻን ለቆ ባህርዳርን የተቀላቀለው ዳዊት መኮንን በ57ኛው ደቂቃ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል፡፡

ኮምቦልቻ ላይ ወሎ ኮምቦልቻ ከ ቡራዩ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ከወጣለት መርሀ ግብር በአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን ጨዋታውም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቆል፡፡ አብዱልከሪም ከድር በ21ኛው ደቂቃ ቡራዩን ቀዳሚ ሲያደርግ ሳሙኤል በለጠ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ኮምቦልቻን አቻ አድርጓል፡፡ በ45ኛው ደቂቃ በሀይሉ ኃይሉ ቡራዩን በድጋሚ መሪ የሚርገውን ግብ ቢያስቆጥርም በ74ኛው ደቂቃ ላይ መለሰ ትዕዘዙ ወሎ ኮምበልቻ አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያስቻለችውን ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

ሱሉልታ ያያ ሪዞርት ላይ አራዳ ክፍለ ከተማን የገጠመው ሽረ እንዳስላሴ 2-0 አሸንፏል፡፡ ንስሀ ታፈሰ በ18ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን ጎል ሲያስቆጥር በ64ኛው ደቂቃ ኤለልያስ ከበደ የሽረን መሪነት አስተማማኝ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል፡፡

ለገጣፎ ለገዳዲ በሜዳው በጠንካራ አቋሙ ቀጥሎ አዲስ አበባ ፖሊስን 2-0 አሸንፏል፡፡ ጌትነት ደጀኔ በ68ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ግብ ሲያስቆጥር በ88ኛው ደቂቃ እንዳለማው ታደሰ ሁለተኛውን አክሏል፡፡

ባህርዳር ላይ ኢትዮጵያ መድንን ያስተናገደው አማራ ውሀ ስራ 1-0 በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ መጠጋት ችሏል፡፡ አብዱል አዚዝ በ65ኛው ደቂቃ ብቸኛውን የአማራ ውሀ ስራ የማሸነፍያ ጎል ማስቀጠር ችሏል፡፡

አክሱም ላይ በአክሱም ከተማ እና ሰበታ ከተማ መካከል የተካሄደው ጨዋታ በሰበታ ከተማ 2-1 መሪነት ሲካሄድ ቆይቶ በ73ኛው ደቂቃ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወደ ዛሬ ተሸጋግሯል፡፡ ዛሬ ቀሪዎቹ 13 ደቂቃዎች የተካሄዱ ሲሆን ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ጨዋታው በሰበታ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

2 Comments

  1. የመሸሌ እና የባህር ዳር ጉዳይ ምንላይ ደረሰ?

  2. ሰላም ለእናንተ ይሁን ውድ የ soccer Ethiopia አዘጋጆች! የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ሊጠናቀቁ የቀሩትን ፕሮግራሞች ብትገልጹልኝ ደስ ይለኛል
    በተረፈ ዝግጅታችሁ ከማንምና ከምንም በላይ አሪፍ ነው በዚሁ ቀጥሉ!

Leave a Reply