የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አርብ በክልል ከተሞች ሲደረጉ ጅማ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገውን ግስጋሴ አሳምሯል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ጥሏል፡፡
ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ሀላባ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በምድብ ለ ያለውን መሪነት በ5 ነጥብ ልዩነት አጠናክሯል፡፡ ለዘንድሮ የጅማ ከተማ ውጤት ማማር ከፍተኛውን ሚና እየተወጣ የሚገኘው ተመስገን ገብረኪዳን በ15 ደቂቃ የጅማን ወሳኝ የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡
በለዕቱ በጣለው ዝናብ ምክንያት ዘግየት ብሎ የተጀመረው ጨዋታ በሞቀ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት ብቸኛዋን የማሸነፍያ ጎል በ15ኛው ደቂቃ ያገኙት ጅማዎች በተዘራ አቡቴ እና ተመስገን ገብረኪዳን አማኝነት ተጠቃሽ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር፡፡ በአዲሱ አሰልጣኝ ሚልዮን አካሉ እየተመሩ ወደ ሜዳ የገቡት ሀላባ ከተማዎችም በዘካርያስ ፍቅሬ እና ጌታሁን ሽመልስ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡
ከዕረፍት መልስ ሀላባ ከተማ የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው የታጨወቱ ሲሆን በተለይም ተቀይረው የገቡት ፍሬው አለማየው እና ስንታየው መንግስቱ ጎል መሆን የሚችሉ እድሎች አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ የጅማው አሰልጣኝ መኮንን ገ/ዩሐንስ በበኩላቸው ወደ ኃላ አፍግፍገው መጨወትን ሲመረጡ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎች ለመፍጠር ሲጥሩ ታይተዋል፡፡
ከፍልሚያው ወሳኝነት ጨዋታው አንጻር ፍፁም ሰላማዊ ሊባል የሚችል ሲሆን በሁለቱም ደጋፊ መካከል መከባበር የታየበት የዳኞች ውሳኔ ጥንቃቄ የተሞላበት ሆነኖ አልፏል፡፡ ኮሚሽነር ሁነው የተመደቡት የጸጥታ ኮሚቴ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጌታቸው ገብረማርያም በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ያለውን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ጨዋታውን በሰላም እንዲያልቅ የቡክላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ወልቂጤ ላይ ወልቂጤ ከተማ ከፋ ቡናን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ የወልቂጤን ወሳኝ ጎል በ86ኛው ደቂቃ ላይ በተገኘው የፍፁም ቅጣት ምት አማካኝነት ሚካኤል ወልደሩፋኤል አስቆጥሯል፡፡
ወደ ድሬዳዋ የተጎዘው ሀድያ ሆስዕና ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል፡፡ ሀድያ ሆስዕና ቀዳሚውን ጎል በ23ኛው ደቂቃ በቢንያም ገመቹ አማካኝነች በቅጣት ምት ቢያገኝም ዳንኤል ሰለሞን በ45ኛው ደቂቃ ባለሜዳውን ቡድን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ድሬዳዋ ላይ ቀጥሎ በተካሄደው የድሬዳዋ ፖሊስ እና ስልጤ ወራቤ ጨዋታ በጥሩ ግስጋሴ ላይ የሚገኘው ስልጤ ወራቤ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ አፀደቀ ግርማ ለወራቤ ቀዳሚውን ጎል በ30ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር በ75ኛው ደቂቃ ጁሀር መሀመድ ድሬዳዋ ፖሊስን አቻ አድርጓል፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ሙሰፋ ያሲን ያስቆጠረው ግብ እንግዳው ስልጤ ወራቤን አሸናፊ አድርጎታል፡፡
ወደ ነገሌ ቦረና የተጓዘው ነቀምት ከተማ ነገሌ ቦረናን 1-0 በማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ነጥቦች ሰብስቧል፡፡ የነቀምትን ብቸኛ ግብ በ17ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ምኞት ማርቆስ ነው፡፡
ወደ ዲላ የተጓዘው ፌዴራል ፖሊስ ከሜዳው ውጪ ድል ቀንቶት የተመለሰ ሌላው ክለብ ሆኗል፡፡ ቻላቸው ቤዛ በ85ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ፌዴራል ፖሊስ 1-0 እንዲያሸንፍ ሲረዳው በሁለተኛው ዙር አስገራሚ ግስጋሴ ያደረገው ዲላ ከተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ሽንፈት ቀምሷል፡፡
የሳምንቱ ከፍተኛ ውጤት በተመዘገበበት ጨዋታ ሐዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ጅንካ ከተማን አስተናግዶ 4-0 አሸንፏል፡፡ ገና ጨዋታው እንደጀመረ በ3ኛው ደቂቃ በብርሃኑ በቀለ ግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ደቡብ ፖሊሶች በ14ኛው ደቂቃ በናትናኤል ጌታሁን እንዲሁም በ27ኛው ደቂቃ በድጋሚ በብርሃኑ በቀለ አማካኝነት ባስቆጠሯቸው ግቦች በ3-0 በመሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ከዕረፍት መልስ በ73ኛው ደቂቃ ሙህዲን አብደላ የማሳረጊያዋን ጎለል አስቆጥሮ ጨዋታው በደቡብ ፖሊስ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በዚህ ሳምንት ያለ ግብ በተጠናቀቀው የምድቡ ብቸኛ ጨዋታ አርሲ ነገሌን ከሻሸመኔ ከተማ ያገናኘው መርሀ ግብር ነው፡፡