ናይል ቤዚን ፡ መከላከያ እና ሊዮፓርድስ በአንድ አመት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ ይፋለማሉ

ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ በሱዳን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ናይል ቤዚን ቻምፒዮንሺፕ ወደ ሩብ ፍፃሜው መግባቱን ያረጋገጠው መከላከያ ትላንት ምሽት በሱዳኑ አህሊ ሼንዲ 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ አብይ ሞገስ ፣ አዲስ ህንፃ እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተን የያዘው አህሊ ሼንዲ የኢትዮጵውያውን ተወካይ ማሸነፉን ተከትሎ ምድቡን በ6 ነጥብ እና 3 የግብ ልዩነት በአንደኝነት አጠናቋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የጅቡቲውን ድኪህልን 2-1 ያሸነፈው መከላከያ 3 ክለቦችን ከያዘው ምድብ በ3 ነጥብ እና 1 የግብ እዳ 2ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ የጅቡቲው ድኪህል በ0 ነጥብ እና 2 የግብ እዳ ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡

በሌሎች ምድቦች ከምድብ 1 አል-ሜሪክ በ7 ነጥቦች 1ኛ ሆኖ ሲያልፍ የዩጋንዳው ቪክቶርያ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ 7 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ 2ኛ ፤ የደቡብ ሱዳኑ ማላኪያ (በጥሩ ሶስተኛነት) ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል፡፡ ከምድብ 2 ኤ.ኤፍ.ሲ ሊዮፓርድስ ፣ አካዳሚክ ቺቴ እና ምዬባ ሲቲ (በጥሩ 3ኛነት) አልፈዋል፡፡

የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ ቅዳሜ እና እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚጀመር ሲሆን የኢትዮጵያው ተወካይ መከላከያ ከኬንያው ኤ.ኤፍ.ሲ ሊዮፓርድስ ጋር ይጫወታል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮው የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ተገናኝተው የኬንያው ቡድን 4-1 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል፡፡

የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

አርብ 22-09- 2006 – ኤ.ኤፍ.ሲ. ሊዮፓርድስ (ኬንያ) ከ መከላከያ (ኢትዮጵያ)

አርብ 22-09-2006 – አል-ሜሪክ (ሱዳን) ከ አካዳሚክ ቺቴ (ብሩንዲ)

ቅዳሜ 23-09-2006 – ቪክቶርያ ዩኒቨርሲቲ (ዩጋንዳ) ከ ምዬባ ሲቲ (ታንዛንያ)

ቅዳሜ 23-09-2006 – አህሊ ሼንዲ (ሱዳን) ከ ማላኪያ (ደቡብ ሱዳን)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *