ሴቶች ጥሎ ማለፍ | አካዳሚ እና አዳማ ከተማ ለግማሽ ፍፃሜው ማለፋቸውን አረጋገጡ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጥሎ ማለፍ የሩብ ፍጻሜ ሁለተኛ ቀን ውሎ ኢትየጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና አዳማ ከተማ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የሚያሳልፋቸውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

በመጀመሪያው ጨዋታ 08:30 ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ነበሩ፡፡  በጨዋታውም በመጀመሪያው 20 ደቂቃዎች ሁሉም 4 ግቦች የተቀጠሩ ሲሆን ጨዋታውም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የ3-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር በታየበት በዚሁ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቃልኪዳን ተስፋዬ ሁለት ፣ ይመችሽ ተስፋዬ አንድ ማስቆጠር ችለዋል፡፡

በዚህ ውጤት መሠረት በመጪው ሐሙስ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በትላንትናው እለት ጥረትን አሸንፎ ካለፈው ደደቢት ጋር በግማሽ ፍጻሜው የሚገናኝ ይሆናል፡፡

በመቀጠል በ10:30 በእለቱ ተጠባቂ ጨዋታ አዳማ ከተማ ከ ጊዲኦ ዲላ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ተመጣጣኝ የሆነ እና እልህ አስጨራሽ የመሸናነፍ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ የተቆጠረ ጎል አዳማን ለድል አብቅቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ዲላዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ተጋድሎ ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል፡፡

በግማሽ ፍጻሜው አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡

Leave a Reply