ባህርዳር ለእሁዱ ጨዋታ እየተዘጋጀች ነው

ግዙፉ የባህርዳር ስታድየም ለመጀመርያ ጊዜ የሚያስተናገደው የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ሊካሄድ 1 ቀን ብቻ ቀርቶታል፡፡ ስታድየሙ ለጨዋታው ዝግጁ እንዲሆንም ስራዎች መሰራታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የመጫወቻ ሜዳውን ሳር የማስተካከል እንዲሁም መስመሮችን ቀለም የመቀባት ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ትሪቡን የሚገኙ መቀመጫዎች ተከላ እና የብሄራዊ ቡድኑ ዋና ስፖንሰር ዋልያ ቢራ ማስታወቂያዎች በስታድየሙ የተለያዩ ክፍሎች ላይ የማስቀመጥ ስራም እየተካሄደ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲታይ የነበረውን ደቂቃዎች ሲቀሩ ማስተካከያ ስራዎች የመስራት ችግርን ለማስወገድና የማስተካከያ ስራዎች ከጨዋታው በፊት እንዲጠናቀቁ በማሰብ እየተሰሩ ነው፡፡

ከስታድየም ውጪ ደግሞ በከተማው ጎዳናዎች ትልልቅ ሞንታርቦዎችን የጫኑ መኪኖች ለዋልያዎቹ በተዜሙ ሙዚቃዎች ከተማውን ሲያደምቁ ነዋሪውንም ለነገው ጨዋታ ለመታደም የቀኑን መድረስ እየተጠባበቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማልያ በመንገዶች ላይ እየተሸጠ ሲሆን በአንዳንድ አደባባዮች እና ትልልቅ ህንፃዎች ላይም የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾችን ምስል የያዙ ፖስተሮች ተለጥፈዋል፡፡

 

አብርሃም ገ/ማርያም ከባህርዳር

ያጋሩ