አሰልጣኝ ማርት ኑይ በቻምፒየንስ ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስን አይመሩም

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማርት ኑይ ባጋጠማቸው የልብ ችግር ምክንያት ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ በስራ ገበታቸው ላይ አይገኙም፡፡ ሆላንዳዊው አሰልጣኝ በላንድ ማርክ ሆስፒታል ህክምናቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን የጤናቸው ሁኔታ መሻሻል ቢታይበትም ሙሉ ለሙቹ ጤነኛ ሆነው ወደ ስራ ለመመለስ በቂ እረፍት ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ (ማክሰኞ) ከቱኒዚያው ቻምፒየን ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ሲያደርግ ማርት ኑይ ቡድናቸውን በጨዋታው እንደማይመሩ ተረጋግጧል፡፡ በቀጣዩ ሳምንት ግንቦት 20 የዋንጫ ባለቤት መሆኑን ባረጋገጠበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ፋሲል ከተማን ሲገጥምም አሰልጣኝ ማርት ኑይ የማይገኙ ይሆናል፡፡

 

የአሰልጣኝ ማርት ኑይ ረዳቶች የሆኑት ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ ፈረሰኞቹ በቀጣይ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች የሚመሩ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም ቅዱስ ጊዮርጊስ ኤሲ ሊዮፓርድስን በድምሩ 3-0 አሸንፎ ወደ ምድብ ድልድሉ ከገባ በኋላ አሰልጣኝ ኑይ ባለቤታቸው ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ወደ ሆላንድ መጓዛቸው የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *