የ2017 የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝን በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያስተናግድ ይሆናል። ቡድኖቹ በመጀመሪያው የቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎቻቸው እና ኤስፔራንስ ከ ኤቷል ደ ሳህል ጋር ካደረገው የሊግ ጨዋታ በመነሳት የሚከተለውን ታክቲካዊ ምልከታ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
እስካሁን በቻምፒዮንስ ሊጉ ሁለት የቅድመ ማጣሪያ ደርሶ መልስ ጨዋታዎች እና የመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ (በድምሩ 5 ጨዋታዎች) ላይ ግብ ያላስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀገር ውስጥ ሊግ ባደረጋቸው የመጨረሻ አራት ጨዋታዎችም እንዲሁ መረቡ አልተደፈረም። ይህም ከቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ጋር አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው። በተለይም አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ክለቡ ሊዮፓርድስን በመልሱ ጨዋታ ሲያስተናግድ እና በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ማሜሎዲ ሳንዳውንስን ከሜዳው ውጪ ሲገጥም ጥብቅ የሆነ መከላከልን እንደዋነኛ የጨዋታ ስትራቴጂ በመተግበር በመልሶ ማጥቃት ከሚገኙ ዕድሎች ግቦችን ለማግኘት ሲሞክር ታይቷል። በተለይም በሰንዳውንሱ ጨዋታ ላይ ጊዮርጊሶች ከጨዋታው መጀመሪያ እስከመገባደጃው ድረስ ከኳስ ኋላ በመሆን ተጋጣሚያቸው በተፈለገው መጠን ዕድሎችን እንዳይፈጥር አድርገዋል። ይህ አይነቱ የመከላከል አጨዋወት በሙሉ 90 ደቂቃው የተጨዋቾችን የአካል ጥንካሬ እና ትኩረት እንዲሁም የቅርፅ አጠባበቅ ስርዐትን ይጠይቃል። አንድ እና ሁለት ስህተቶች ክፍተቶች ለመቆጣጠር በሚያስቸግር መልኩ ለጥቃት ሊያጋልጡ ስለሚችሉም ተጨዋቾች የግል እንቅስቃሲያቸው በብልጠት እና በጥንቃቄ የተቃኘ እንዲሆን ግድ ይላል። ከተጨዋቾች የግል እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑ የተከላካይ ፣ የአማካይ እና የአጥቂ ክፍሎች /Departments/ በተለይ ወደ መከላከል በሚደረጉ ሽግግሮች ወቅት ትክክለኛውን ቦታ መያዛቸው ብቻ ሳይሆን ወደዛ ቅርፅ ለመግባት የሚፈጅባቸው ጊዜም ተጋጣሚያቸው ኳሱን ወደ አደጋ ክልል ለማድረስ ከሚፈጅበት ጊዜ ያነሰ ሊሆን ይገባል።
በእርግጥ የመከላከል ስራውን ሊያከብደው እና ሊያቀለው የሚችለው የተጋጣሚ የማጥቃት ስትራቴጂ ጥንካሬ እና የጨዋታው ፍጥነት ነው። በሰንዳውንሱ ጨዋታ ላይ ባለሜዳው ቡድን የመስመር ተከላካዮቹን በማጥቃቱ ላይ በብዛት በማሳተፍ እና የሜዳውን ስፋት በሚገባ ለመጠቀም ሲጥር ተስተውሏል። በጨዋታው 92% የሚሆነው የቡድኑ ጥቃትም ይነሳ የነበረው ከሁለቱ መስመሮች ነበር። በጨዋታውም የሰንዳውንስ የመሀል ለመሀል ጥቃት አናሳ መሆኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አማካዮች ራምኬል ሎክ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በተጨማሪ ከተከላካይ መስመሩ ፊት የተሰለፉት ናትናኤል ዘለቀ እና ተስፋዬ አለባቸውም የመስመር ተከላካዮቻቸውን እንዲያግዙ ረድቷቸዋል። በዚህም ሁኔታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመስመሮች በኩል ከተሰነዘሩበት 56 ጥቃቶች ግቦች እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ችሏል። ያም ቢሆን የቡድኑ የመከላከል አጨዋወት ሙሉ ለሙሉ ከስህተት የፀዳ ነበር ማለት አይቻልም። በተለይም በሜዳው ቁመት በተከላካይ እና በአማካይ መስመሩ መሀከል ያለውን ክፍተት በፍጥነት በማጥበብ በኩል እና በተጨዋቾች ትክክለኛ ቦታ አያያዝ ላይ ስህተቶች ይታዩ ነበር። በምስሉ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃት ላይ ይሳተፍ ከነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ላንገርማን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል የጣለውን ኳስ ያሳየናል፡፡
ይህ ኳስ የሳንዳውንሶችን የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ኳሱ ወደ ሳጥኑ በተሻማበት ወቅት 7 የሚሆኑ የጊዮርጊስ ተጨዋቾች በሳጥኑ ውስጥ እና ዙሪያ ቢታዩም አደገኛ አቋቋም ላይ የነበሩትን ሁለት የሳንዳውንስ አጥቂዎች ግን ነፃ ሆነው እናገኛቸዋለን። የቀኝ መስመር ተከላካዩ አስቻለው ታመነ እና የመሀል ተከላካዩ ሳላዲን ባርጌቾ እንዲሁም ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ናትናኤል እና ተስፋዬ ከአጥቂዎቹ ጀርባ ሆነው ሲታዩ አበባው እና ደጉ ኳሱን ለመቀበል የመጀመሪያ ከሆነው ተጨዋች ጋር ኳስ ለማስጣል ይሞክራሉ።
እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች የጨዋታውን ሂደት ሙሉ ለሙሉ የመቀየር አቅም ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይሻሉ። በመሆኑም ቡድኑ በመከላከል ወቅት በሽግግሮች ላይ በሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ላይ በተለይም ከመስመር ኳሶች በሚነሱበት ወቅት የተጨዋቾች ቦታ አያያዝ ፍጥነት እና ትክክለኛነት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል። በእርግጥ ሳንዳውንሶች በጨዋታው ከ3 በላይ ዕድል እንዳይፈጥሩ መሆኑ የቅዱስ ጊዮርጊስን የመከላከል አጨዋወት ውጤታማ እንደነበር የሚነግረን ነው። እዚህ ላይ በጨዋታው 18 ኳሶችን በማቋረጥ ከሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች የተሻለ ቁጥር ያስመዘገበውን የአምበሉን ደጉ ደበበን ሚና መጥቀስም ተገቢ ነው። ይህም ከቡድን አደረጃጀቱ ሌላ የተጨዋቾች የግል ብቃት እና ትኩረት ተመሳሳይ አደጋዎች ወደግብነት እንዳይቀየሩ እንደሚረዳ ያሳየናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ነገር ቢያሳይም በጨዋታው ማድረግ የቻለው ግን አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ነበር። በእርግጥ ቡድኑ ለጨዋታው ከቀረበበት መንገድ አንፃር ኳስ በሚነጥቅበት ወቅት አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች በራሳቸው ሜዳ ላይ መገኘታቸው በማጥቃት ሽግግር ውስጥ የቁጥር ብልጫን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ለመፍጠር ብዙ ርቀቶችን የመሸፈን ግዴታ ውስጥ ከቷቸው ነበር። ሆኖም ግን በዚሁ ጨዋታ ላይ ጊዮርጊሶች ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት ወቅቶች ቢፈጠሩላቸውም ኳስ ማቀበያ አማራጮች ባለመኖራቸው እና የመልሶ ማጥቃቱን የሚያስጀምራቸው ተጨዋች በሚፈጥረው የቅብብል ስህተት ሳቢያ ሳንዳውንሶች የመከላከል ሽግግራቸውን በማጠናቀቅ እና ቅርፃቸውን ፈጥነው በመያዝ ሲይመክኗቸው ታይቷል። እነዚህ አጋጣሚዎችን ወደግብ ዕድል ለመቀየር መልሶ ማጥቃቱን ሚያስጀምረው ተጨዋች ኳስን በአንድ አቅጣጫ ከመግፋት ይልቅ ጥሩ አቋቋም ላይ ላለ ተጨዋች ቢያሳልፍ የተሻለ ነው። ምክንያቱም ማጥቃቱን የሚያስጀምረው ተጨዋች ከኳስ ጋር ብዙ በሮጠ ቁጥር ያለኳስ በመሮጥ ሊደርሱበት ለሚሞክሩት ተከላካዮች ጊዜን ይሰጣል። ይህም የተጋጣሚን የመከላከል ሽግግር የሚያግዝ ይሆናል። ከታች የሚታዩት ሁለት ምስሎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ለቀኝ መስመር አምካዩ ራምኬል ተልከው የነበሩ እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን የፈጠሩ አጋጣሚዎች ናቸው ።
በሁለቱም አጋጣሚዎች ከተጫዋቹ በስተግራ አብዱልከሪም ኒኪማ ቀጥተኛ ሩጫዎችን ሲያደርግ ይታያል። ሆኖም ራምኬል ኳስ በመግፋት ወደ ሰንዳውንስ የግብ ክልል ለመሄድ ብዙ ርቀት ሲሮጥ በመጀመሪያ ከሱ በተወሰኑ ሜትሮች ወደኋላ ሆኖ ይታይ የነበረ ተጨዋች ያለኳስ በመሮጥ ደርሶ ያስጥለዋል። እነዚህ አጋጣሚዎች ከተጨዋቾች የግል ስህተቶች በላይ የቡድኑን የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ይሆናሉ። በተለይም ቡድኑ ከሚታወቅበት የመስመር እንቅስቃሴ አንፃር በጨዋታው ከመስመር ወደ አደጋ ክልል መላክ የቻላቸው ኳሶች ቁጥር አምስት ብቻ መሆናቸው እና ከአምስቱ ሁለቱ የተነሱት በአስር ቁጥር ቦታ ላይ ከተሰለፈው ንኪማ እንጂ ከመስመር ተሰላፊዎቹ አለመሆኑ እንዲሁም ከእነዚህም ስኬታማ የነበረው አንዱ ብቻ መሆኑ ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክር ነው። በመሆኑም ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች በሚፈጠሩበት ወቅት ጥቃቱን የሚያስጀምሩት ተጨዋች ኳስ ሊቀበሏቸው የሚችሉ እና የሜዳውን ስፋት ሊያስጠቅም በሚችል ርቀት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ወደተጋጣሚ ሜዳ እንዲገቡ የሚይስችል ዕቅድ ያስፈልገዋል። ጥቃቱን የሚያስጀምሩ ተጨዋቾችም የመጀመሪያ ተግባራቸው እናዛን ተጨዋቾች በቀጥተኛም ሆነ በጎንዮሽ ቅብብል ማግኘት መሆን ይገባዋል። ቅብብላቸውም የፍጥነት እና የስኬት ችግር ሳይገጥማቸው እና የተጋጣሚያቸው የመከላከል ሽግግር ሳይጠናቀቅ ለመጨረሻ ዕድል መፈጠሪያነት ሊውሉ የሚገባቸው ናቸው።
ከ2010 ጀምሮ በነበሩት ሶስት ተከታታይ አመታት በቻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ መድረስ የቻለው የቱኒዚያው ክለብ ኤስፒራንስ በ 2011 የውድድር አመት አሸናፊ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው። ክለቡ በሁሉም ውድድሮች ያደረጋቸውን የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ በድል ሲያጠናቀቅ በአማካይ በጨዋታ 2.3 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በነዚህ ጨዋታዎችም በቻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ኤ ኤስ ቪታ ካስቆጠረበት አንድ ግን ውጪ ሌላ ጎል አላስተናገድም። ይህም ወቅታው አቋሙ በምድቡ ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች ውስጥ ጠንካራው እንደሆነ የሚጠቁም አይነት ነው። የያዝነው የ2017 አመት ከተጀመረ ወዲህም የቱኒዙ ክለብ የገጠመው ሽንፈት ሁለት ብቻ መሆኑ እና ባሳለፍነው ሳምንት የቱኒዚያ ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን ማረጋገጡ ቡድኑ ጥሩ የማሸነፍ ስነልቦና ላይ እንዳለ የሚጠቁም ነው።
ክለቡ የያዛቸው ተጨዋቾች በግል ተሰጥኦም ሆነ በቡድን አደረጃጀት ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከኳስ ውጪ በሚሆኑበት ወቅት ከፊት በሚጠቀሙት አንድ አጥቂ እና ከበስተጀርባው በሚሰለፉ ሶስት አማካዮች አምካይነት ተጋጣሚን በራሱ ሜዳ ላይ በከፍተኛ ጫና ውስጥ የመክተት አጨዋወትን ይከተላሉ። ይህ ጫና /pressing/ ወደመሀል ሜዳው ቀርቦ ከሚጫወተው የተከላካይ መስመራቸው ጋር ሲቀናጅ በሜዳው ቁመት በተጫዋቾች መሀል ያለው ርቅት የተመጠነ እንዲሆን እና ተጋጣሚ ኳስ በቀላሉ እንዳይመሰርት የሚያደርግም ነው። ከተከላካይ መስመሩ ፊት የሚሰለፉት ሁለት አማካዮችም ኳስ በማጨናገፍም ሆነ ማጥቃቱን በማስጀመር በኩል የተሳካላቸው ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን የቡድኑ የመስመር አማካዮች አጨዋወት ዋነኛ ጥንካሬው ነው ማለት ይቻላል። በመከላከል ወቅት ወደኋላ በመመለስ ከመስመር ተከላካዮቻቸው ጋር ያለው ርቀት በማጥበብ እና ወደተከላካይ አማካዮች በመቅረብ መስመሮችን የሚዘጉበት መንገድ የተጠናና እና በሁለቱም ሽግግሮች ወቅት ሚዛኑን የጠበቀ ነው። በተለይ ከግራ መስመር የሚነሳው ፋክረዲን ቤን የሱፍ ተጨዋቾችን በማለፍ ወደውስጥ የመግባት ችሎታ እና ፍጥነት አንዱ የቡድኑ ጠንካራ የግብ ዕድል መፍጠሪያ አማራጭ ነው። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የፊት አጥቂው ጣሀ ያሲን ኬናሲም ሰፊ ሜዳን አካሎ የሚጫወት እና ከአማካይ መስመሩ ጋር በቅርበት የሚገናኝ መሆኑ ለተጋጣሚዎች በቀላሉ ለመያዝ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በጥቅሉ ኤስፔራንስ በጥቂት ንክኪ ኳሶችን ወደፊት በማድረስ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥር አይነት ቡድን ነው። ከጥልቅ አማካይ እና ከተከላካይ መስመር የሚነሱት ኳሶችም የመስመር አማካዮቹ በሚያደርጓቸው ቀጥተኛ ሩጫዎች አማካይነት መድረሻቸውን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ያደርጋሉ። በዚህ ረገድ የማጥቃት ሽግግራቸው ፈጣን ከመሆኑ በተጨማሪ ከመስመሮቹ ጋር መሀል ለመሀል የሚደረጉ ጥቃቶችንም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ለዚህም የቡድኑ ፈጣሪ ተጨዋች የሆነው አኒስ ባድሪ ከጠንካራዎቹ የተከላካይ አማካዮች ፊት እና ከአጥቂው ጀርባ ባለው ቦታ ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠቃች ነው። ከቪታ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ ቡድኑ ማጥቃት ከሰነዘረባቸው ጊዜያቶች 81% የሚሆነው በግራ እና በቀኝ በኩል ከተነሱ እንቅስቃሴዎች ነበር። ከዚህም በመነጨ 24 የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ 12ቱ ኢላማቸውን የጠበቁ ነበሩ። ምንም እንኳን የሶስት ተጨዋቾች ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ቢጀምሩም ሀሙስ ኤቷል ደ ሳህልን 3-0 በረቱበት ጨዋታ በተመሳሳይ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቁጥር ቢያስመዘግብም ፈጣን የማጥቃት ሂደት እና ንክኪ ያልበዛባቸው የሜዳውን አብዛኛውን ክፍል በጥቂት ድግግሞሽ ውስጥ ያለስህተት ማቋረጥ በሚችሉ ኩሶች በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ መቻሉ ይበልጥ አስፈሪ ያደርገዋል።

በሜዳ ላይ ሁሉም መለኪያዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጀመሪያ ተጋጣሚው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ አንፃር የቱኒዙ ክለብ ጥንካሬ የጎላ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስም ከፕሪቶሪያው ጨዋታ አንፃር በመጠኑ የማጥቃት አዝማሚያ ያሳያል ተብሎ በሚጠበቅበት ጨዋታ ላይ ከምንም በላይ በራሱ ሜዳ የሚያደርጋቸውን ቅብብሎች ስኬታማነት ማጤን ይገባዋል። ምንም እንኳ የኤስፔራንሶች በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ከባድ ጫና የመፍጠር አጨዋወት መጠኑ በአዲስ አበባ ስታድየም አልቲቲውድ ምክንያት ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን አይኖርም ማለት ግን አያስደፍርም። ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ መስመሮቹን የሚዘጋበትን መንገድ በፍጥነትም ሆነ ክፍተትን ባለመስጠት የተጠና መሆን አለበት። የመስመር አማካዮች የኋልዮሽ እንቅስቃሴም ለዚህ ክንውን ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። ከተዘረዘሩተ ነጥቦች ሌላ ኤስፒራንሶች ከቆሙ ኳሶች በተለይም ከማዕዘን ምት ና ከግቡ ጎኖች ከሚነሱ የቅጣት ምቶች ዕድሎችን ለመፈጠር የሚያስችል ቁመና እና ፍጥነት የታደሉ ናቸው፡፡ ስለዚህም ጊዮርጊሶች እነዚህን አጋጣሚዎች በትኩረት መከላከል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የሳላዲን ሰይድ መመለስ ለፈረሰኞቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ ተጨዋቹ ካለው ልምድ እና ከወቅታዊ አቋሙ ባለፈ ፍጥነቱ እና ሰፊ ሜዳ አካሎ የሚጫወት አጥቂ መሆኑ ከአማካይ መስመር የሚላክለትን ኳስ ከኤስፒራንስ የተከላካይ መስመር ጀርባ ይዞ ለመግባት እንደሚያስችለው ይታመናል፡፡