ማክሰኞ የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝን በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የሚያስተናግደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ከሰዓት ጨዋታውን በሚያደርግበት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል፡፡
ሆላንዳዊው የፈረሠኞቹ አሰልጣኝ ማርት ኖይ በህመም ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ በምክትል አሰልጣኞቹ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ ነበር ልምምዱ የተመራው፡፡ 25 ተጫዋቾች በተሳተፉበት ልምምድ የቆመ ኳስ አጠቃቀም፣ ከ16.50 ውጪ በግቡ ትይዩ የቅጣት ምት ልምምድ፣ በግማሽ ሜዳ የቦታ እና ክፍተት አጠቃቀም ልምምዶችን ፈረሰኞቹ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡
በጉዳት ላይ የነበረው የመስመር አማካዩ በኃይሉ አሰፋ በልምምዱ ላይ ቢሳተፍም ለጨዋታው ግን ዝግጁ አለመሆኑን ተከትሎ ከጨዋታው ውጪ ነው፡፡ ለረጅም ግዜ በጉዳት የተለየው ተከላካዩ አሉላ ግርማ ቀላል ልምምዶችን ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታው ላይ የሚሳተፉ የ18 ተጫዋቾችን ስም ዝርዝር ነገ ማለዳ ላይ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡