ኢትዮጵያ ቡና እና አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች በይፋ የውል ስምምነት ተፈራረሙ 

ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ረፋድ በክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ይፋ ባደረገው መሰረት ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ኢትዮጵያ ቡናን እንደ ሁኔታው ሊራዘም በሚችል የአንድ አመት የውል ስምምነት ክለቡን ለማሰልጠን በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሆቴል በተጠራ ስነስርአት ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ክለቡን በመወከል ስራ አስኪያጁ አቶ በላይ እርቁ እንዲሁም የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት የሆኑት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ተገኝተዋል፡፡

ፕሮግራሙን በንግግራቸው የከፈቱት ክለቡ ስራአስኪያጅ አቶ በላይ እርቁ በንግግራቸው የክለባቸው ዋንኛ እቅድ የሆነውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን የመሆንና በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የመሆን እቅድን ለማሳካት ቡድኑ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ መቅጠሩን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በክለቡ ዘንድ ፖፓዲችን ስለመረጡበት መስፈርት ሲያስረዱ አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም በ2008 ዓ.ም ቡድኑን በማሰልጠናቸው ቡድኑ ስለሚያቁትና በቆይታቸውም የነበራቸው አጠቃላይ የቡድን እንቅስቃሴና ውጤት ጥሩ መሆኑ ቡድኑ ዳግም አሰልጣኝ ፖፓዲችን ወደ መንበሩ እንዲመልሱ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከአቶ በላይ ንግግር በኃላ በአሰልጣኙና በክለቡ ስራ አስኪያጅ አማካኝነት የተዘጋጀው የውል ስምምነት ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ በመቀጠል የክለቡ የቦርድ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች የሚከተሉትን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

ስለ አሰልጣኞች መለዋወጥና ረጅም ጊዜ እቅድ

“የአሰልጣኞች ሹምሽር እና የረጅም ጊዜ እቅድ አለመኖር የተለያዩ ጉዳዬች ናቸው፡፡ አሰልጣኝ ኒቮሳ ቩሴቪች የተቀጠሩት ቡድኑን በጥሩ ውጤት እንዲያስጉዙ ነበር፡፡ ነገር ግን የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማምጣታቸው ልናሰናብታቸው ተገደናል፡፡ እንደውም ውጤታቸውን ተመልክተን በማሰናበታችን ልንመሰገን ይገባል፡፡ በመቀጠል ወደ ቦታው የመጡት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ቡድኑን በቀሩት ጨዋታ አሻሽለው ወደ ሊጉ ዋንጫ እንዲመሩ ነበር ፤ ነገርግን ይህም ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህ ገዛኸኝ ያለውን እድል ተጠቅሟል ፤ በቀጣይ ቡድኑ የቀረው ብቸኛ የአፍሪካ ውድድር ህልሙን ለማሳካት የጥሎ ማለፍ ውድድር ስለሆነ በዚህ ደግሞ የገዛኸኝ ረዳት ለነበረው አሰልጣኝ እድሉ ደረጀ ደግሞ በተራው እድል ሰጥተነዋል፡፡”

 

ስለቀድሞው የቡድኑ ስራ አስኪያጅ በዚህ ቅጥር ላይ እጃቸው አለ ስለመባሉ

 

“እሳቸው ህገ-መንግስቱ በሰጣቸው እድል በመጠቀም እንደማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ መብታቸውን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከቡድኑ ጋር ስለተለያዩ ዳግም ከቡድኑ ጋር መስራት አይችሉም ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በዚህ ቅጥር ላይ እጁ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል፡፡”

ስለአሰልጣኝ ቡድናቸው አወቃቀር

“በቡድናችን ከዋናው የወንዶች ቡድን እስከታዳጊዎች እንዲሁም በሴት ቡድን ውስጥ የተለያዩ አቅም ያላቸው አሰልጣኞች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ አሰልጣኙ ከነዚሁ አሰልጣኞች የመምረጥ መብት አላቸው፡፡”

 

በአዲሱ የአሰልጣኙ ኮንትራት ላይ ከዚህ ቀደሙ የተሻሻሉ ነገሮች ካሉ

” በተወሰኑ ጨዋታዎች ውጤት ካልተገኘ ሊሰናበቱ እንደሚችሉ ፣ በማኔጅመንቱ ስራ ላይ ችግር ካለ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይችላሉ እንዲሁም ከውጤት ጋር በተያያዘ ጉርሻ የማግኘት መብት በአዲሱ ኮንትራት ላይ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡”

 

ስለ ካሳዬ አራጌ

” ከካሳዬ አራጌ ጋር ተገናኝተን ተወያይተናል በንግግራችንም እንደተረዳነው አሜሪካ ሀገር ከሄደ በኃላ ምንም አይነት የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዳልወሰደና ነገርግን አሁን ላይ የጀመረውን የአሰልጣኝነት ኮርስ እንዳለና እሱን መጨረስ እንደሚፈልግ ነገሮናል በተጨማሪም በኛ በኩል እንደሀሳብ ያቀረብንለት በቀጣይ የጀመረውን ኮርስ ሲጨርስ

አሜሪካ ወይም በአውሮፓ በመሄድ የአለም እግርኳስ የደረሰበትን የሳይንስ ማለትም የUEFA PRO LICENCE ደረጃ ተመዝግቦ እንዲማር ካልሆነም ለመማር ወጪውን መሸፈን ካልቻለ ክለቡን እንደሚሸፍንለት ተነጋግረን ተለያይተናል፡፡”

 

በቀጣይ ክለቡ ፊቱን ወደ ሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ስለመመለስ

“የኢትዮጵያ እግርኳስ ፈደሬሽን የአሰልጣኞች አሰለጣጠን መንድን  እስካልተስተካከለ ድረስ ወደ ኢትዮጽያ አሰልጣኞች ዳግም አንመለስም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *