በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ዙርያ ከቱኒዝያዊ ጋዜጠኛ ጋር የተደረገ ቆይታ

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራንስ ጋር ይጫወታል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር አቻ ተለያይተው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡት ፈረሰኞቹ ማክሰኞ የቱኒዚያውን አዲስ ቻምፕዮን የሚያስተናግዱበት ጨዋታም ተጠብቋል፡፡

መቀመጫውን ክርምሎንት ፈረንሳይ ያደረገው ቱኒዚያዊው ጋዜጠኛ ኦልዋዳ ሎትፊ ትኩረቱን ለአፍሪካ እግርኳስ በማድረግ ይታወቃል፡፡ በ2016 የካፍ ግሎ ሽልማት ላይ በሚዲያ ፓናል ኤክስፐርትነት ያገለገለው ሎትፊ ስለኤስፔራንስ ወቅታዊ ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

በቅርብ አመታት ላይ ኤስፔራንስ በአፍሪካ መድረክ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ ወደ ምድብም መግባት ሲቸግረው አይተናል፡፡ አሁን ላይ ምን ተለወጠ?

“በአጠቃላይ ሁለት ነገሮች ናቸው የተለወጡት፡፡ በጥራታቸው ላቅ ያለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን በተለይም በ2014 እና 2015 የነበረው የቡድን ስብስብ ላይ አለመኖር እና ሁለተኛው ከቡድን ይልቅ በግለሰቦች ላይ ቡድኑን የመጠንጠል ሁኔታ ይታይበት ነበር፡፡ አሁን ላይ ሁለቱን ነገሮች ቀርፈዋል፡፡ በየቦታው ጥራት እና ችሎታ ያላቸው እንዲሁም እንደቡድን የሚጫወት ኤስፔራንስን አሰልጣኝ ፋውዚ ቤንዛርቲ እየፈጠሩ ነው፡፡”

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ቡድኑ በጨዋታ እንቅስቃሴ ተበልጦም ለማሸነፍ ሲቸገር አይስተዋልም፡፡ ቡድኑ በመልሶ ማጥቃትም ላይ አደገኛ ነው፡፡ ይህ ምንአልባት ከፋውዚ ቤንዛርቲ ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ ከመምጣት ጋር ይያያዛል?

“ለእኔ ከተጫዋቾቹ ካላቸው ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ይያያዛል፡፡ አጥቂዎቹ እና አማካዮቹ አሁን ላይ ያለኳስ ያላቸው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው፡፡ አሰልጣን ንጄንግ እያለ ከነበረው እጅግ በጣም የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ ቤንዛርቲ በኤስፔራንስ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ላይ አሻራውን አሳርፏል፡፡ በመልሶ ማጥቃት ወቅት ቡድኑ ያለውን የመከላከል አደረጃጀት እንዲያሻሻል በማድረግ ቡድኑ ኳስ ቢቀማ እንኳን ተከላካዮች በተገባ ቦታቸው እዲገኙ የፋውዚ ቡድኑን መምራት እረድቷቸዋል፡፡”

በውድድር ዓመቱ ላይ ኤስፔራንስ ወሳኝ ተጫዋቾቹ የነበሩት እንደ ሳሲ፣ ቤን የሱፍ፣ ኬኔሲ፣ ኩሊባሊ እና ምባረኪ ያሉት አብዛኛውን ግዜ በቋሚነት የሚጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ለአንተ የኤስፔራንስ ወሳኝ ተጫዋች ማነው?

“በግሌ እንደማስበው ጠሃ ያሲን ኬኔሲ አሁን ላይ የኤስፔራንስ ብቻ ሳይሆን የቱኒዚያ ምርጡ የፊት መስመር ተሰላፊ ነው፡፡ የኤስፔራንስ ዋነኛ የግብ ምንጭም ነው፡፡ በሌላ በኩል ከኬኔሲ በመቀጠል ብጨምር የቡድኑ ሶስቱ የመሃል አማካዮች የኤስፔራንስ ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው ፡፡ በሴፋክሲየን የተጫወተው ፈርጃኒ ሳሲ፣ ከኤስፔራንስ ወጣት ቡድን ያደገው ጋይለን ቻላሊ እና ጠንካራው ፎሶኒ ኩሊባሊ የፋውዚ ቤንዛርቲን ጫና ፈጥሮ የመጫወት ታክቲክ በሚገባ የሚያስፈፅሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡”

ኤስፔራንስ ያለጥርጥር አማካይ ክፍሉ ዋነኛ ጥንካሬው ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

“እስማማለው፡፡ የኤስፔራንስ ጥንካሬ አማካዩ ነው፡፡ ጥሩ የቴክኒክ ብቃት፣ የአካል ብቃት ጥንካሬ እና ፍጥነትን የተላበሱ ተጫዋቾች የያዘ ነው፡፡ ቀይ እና ወርቃማዎቹ ኳስን ሲነጠቁ ፋውዚ ቤንዛርቲ የሚወዱትን ያለኳስ ጫና ፈጥሮ የመጫወት ታክቲክ በሚገባ ቡድኑ ይተግብራል፡፡ ይህ ዋነኛ የኤስፔራንስ ጥንካሬ ነው፡፡ የተለያዩ ባህሪ ያላቸውን የፊት መስመር ተሰላፊዎች የያዘ ቡድን መሆኑ ሌላው ጥንካሬ ነው፡፡ ፋክረዲን ቤን የሱፍ፣ አኒስ ባድሪ፣ አደም ሬጃቢ፣ ሰዓድ ብጉር እና ዋነኛ የግብ ምንጫቸው ጠሃ ያሲን ኬኔሲ የያዘ ስብስብ ነው፡፡”

ኤስፔራንስ እንደ አማካዩ እና አጥቂው ጥንካሬ የተከላካይ ክፍሉ እምብዛም ጠንካራ አይደለም. . .

“ምንም እንኳን መሻሻልን ቢያሳይም እና በ10 ጨዋታዎች 2 ግቦችን ብቻ ቢያስተናግድም አሁንም የኤስፔራንስ ድክመት የተከላካይ ክፍሉ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውን የኤኤስ ቪታ ክለብ አጥቂ ያዚድ አቶባ በቻምፒየንስ ሊጉ ያስቆጠረውን መመልከት በቂ ነው፡፡ የመስመር ተከላካዮቹ ካሊል ሸማም እና ኢሃብ ምባረኪ ወደ ተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክልል ገብተው ማጥቃቱን ማገዝ ይወዳሉ፡፡ ይህ ሲያደርጉ ክፍተት ትተው መሄዳቸው እና ክፍተቱን የሚሸፍን ተጫዋች በቦታው አለመገኘቱ ሌላው ድክመት ነው፡፡ ግብ ጠባቂው ሞይዝ ቤን ሻሪፋ ጥሩ ብቃት ላይ ሆኖ ጥፋት ይሰራል፡፡ በረጅም ግዜያት አድካሚ እየሆነ የሚመጣው የፋውዚ ቤንዛርቲ ጫና ፈጥሮ የመጫወት ታክቲክም ሌላው የኤስፔራንስ ራስ ምታት ነው፡፡”

ኤስፔራንስ ዘንድሮ የሊጉን ክብር ማሳካት ችሏል. . .

“የተገባ ድል ነው፡፡ አብዛኞቹ ጨዋታቸውን በድል ተወጥተዋል ፤ ምንም እንኳን በመጀመሪያው ዙር በጨዋታ እንቅስቃሴ አሳማኝ ባይሆኑም፡፡ የቤንዛርቲ ጥር ላይ መምጣት ብዙ ነገሮችን ለውጧል፡፡ በሁለተኛው ዙር ጥሩ እግርኳስን መጫወት ችለዋል፡፡ የሊግ ዋንጫውንም ማሸነፍ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ለዋንጫ ከሚፎካከሯቸው ጋር በነበራቸው የእርስ በእርስ ግንኙነትም እጅግ በጣም የተሻሉ ነበሩ፡፡ በቱኒዝ ደርቢ ከክለብ አፍሪኬን እንዲሁም ከኤቷል ደ ሳህል እና ሲኤስ ሴፋክሲየን ጋር የነበራቸውን ጨዋታ በበላይነት ጨርሰዋል፡፡”

Leave a Reply