ቻምፒየንስ ሊግ | የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

በ2017 ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ በአምስት የአፍሪካ ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀምራሉ፡፡

ምድብ ሀ

በዛሬው መርሃ ግብር ከፍተኛ ግምትን ያገኘው ጨዋታ ኤል ሜሪክ ኤቷል ደ ሳህልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ነው፡፡ ሜሪክ በሱዳን ፕሪምየር ሊግ ከመሪው አል ሂላል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነትን ማጥበብ ባይችልም ከኦምዱሩማን ባላንጣው ጋር በቻምፒየንስ ሊጉ ከሜዳው ውጪ ያደረገውን ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቅቋል፡፡ የቱኒዚያ ሊግ 1 ክቡሩን ዳግም ሳያሳካ በኤስፔራንስ 3-0 ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣው የሁበርት ቩሉዱ ኤቷል ደ ሳህል በመጀመሪያው ጨዋታ ሳይቸገር ፌሮቫያሪዮ ቤይራን 5-0 ረምርሟል፡፡

አል ሂላል ወደ ማፑቶ አቅንቶ ፌሬቫያሪዮ ቤይራን ይገጥማል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በሰፊ ግብ የተሸነፈው የሞዛምቢኩ ክለብ በሜዳው ኢስታዲዮ ናሲዮናል ዶ ዚምፔቶ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ለማሸነፍ ፈታኝ ነው፡፡

ምድብ ለ

በምድቡ ብቸኛ ጨዋታ ሴፋክስ ላይ አል አሃሊ ትሪፖሊ ዛማሌክን ያስተናግዳል፡፡ በሊቢያ ባለው ያለመረጋጋት የሜዳ ላይ ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ የተገደደው አሃሊ ትሪፖሊ በምድቡ መክፈቻ ጨዋታ በዩኤስኤም አልጀር 3-0 ተሸንፏል፡፡ የአምስት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ዛማሌክ በመጀመሪያው ጨዋታ ካፕስ ዩናይትድን 2-0 ረቷል፡፡ ዛማሌክ ከተጋጣሚዊ በተጫዋቾች ጥራት መብለጡን እንዲሁም በገለልተኛ ሜዳ ቱኒዚያ ላይ ጨዋታው መደረጉን ተከትሎ የማሸነፍ ቅድመ ግምቱን አግኝቷል፡፡

ምድብ ሐ

በዚህ ምድብም በተመሳሳይ ዛሬ አንድ ጨዋታ ይደረጋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲሱን የቱኒዚያ ቻምፒዮን ኤስፔራንስ ያስታናግዳል፡፡ ሁለቱም ክለቦች የሃገራቸውን ሊጎች በተመሳሳይ ቀን ባሳለፍነው ሐሙስ ማሸነፋቸውን አረጋግጠው ነው ለጨዋታው የቀረቡት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ጨዋታ ፕሪቶሪያ ላይ የወቅቱ ቻምፒዮኑን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ገጥሞ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ኤስፔራንስ ቱኒዝ ቪታ ክለብ 3-1 በመርታት የምድቡ መሪ ነው፡፡ ኤስፔራንስ የኢትዮጵያ ክለብ ሲገጥም ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡

ምድብ መ

የስምንት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አሃሊ ጋሮአ አቅንቶ የካሜሮኑን ኮተን ስፖርት ይገጥማል፡፡ ሁለቱም ክለቦች በመጀመሪያ ጨዋታቸው ነጥብ በመጣላቸው ሶስት ነጥብ ማሳካት የግድ ይላቸዋል፡፡ አል አሃሊ እና ኮተን ስፖርት በቻምፒየንሰ ሊጉ ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ አይደለም፡፡ በ2008 የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ተገናኝተው አል አሃሊ በአጠቃላይ ውጤት 4-2 አሸንፎ ለስደስተኛ ግዜ ዋንጫውን አንስቷል፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

09፡00 – ክለብ ፌሮቫያሪዮ ዳ ቤይራ ከ አል ሂላል

10፡00 – ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ

10፡00 – ኮተን ስፖርት ከ አል አሃሊ

01፡00 – አል አሃሊ ትሪፖሊ ከ ዛማሌክ

03፡00 – ኤል ሜሪክ ከ ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *