በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ዛሬ የአራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ በአራት የአፍሪካ ከተሞች በሚደረጉት ጨዋታዎች ቀጥሎ የሚውለው ኮንፌድሬሽን ዋንጫው ረቡዕ ቀሪ አራት ጨዋታዎች የሚደረጉበት ይሆናል፡፡

ምድብ ሀ

የዩጋንዳው ኬሲሲኤ የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካን ያስተናግዳል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ኬሲሲኤ በፉስ ራባት የተሸነፈ ሲሆን የቱኒዚያ ሊግ 1 በሶስተኝነት ያጠናቀቀው ክለብ አፍሪካ ሪቨርስ ዩናይትድን ድል አድርጓል፡፡ ኬሲሲኤ ባሳለፍነው ሳምንት የዩጋንዳ አዛም ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን በጉዳት ላይ የነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ መመለሳቸው ፊሊፕ ኦሞንዲ ላይ በሚደረገው ጨዋታ የተሻለ ግምትን እዲያገኝ አስችሎታል፡፡

ምድብ ለ

ሁለቱም የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ የሰሜን አፍሪካ እና የደቡባዊ አፍሪካ ክለቦች ፍጥጫ ተጠብቋል፡፡ ከደቡባዊ አፍሪካ የተገኙት የስዋዚላንዱ ምባባኔ ስዋሎስ እና የደቡብ አፍሪካው ፕላቲኒየም ስታርስ ሲፋጠጡ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ አልጀርስ ላይ ኤምሲ አልጀር ሴፋክሲየንን ያስተናግዳል፡፡ ምባባኔ ስዋሎስ በመጀመሪያው ጨዋታ በሴፋክሲየን በጠባብ ውጤት ሲሸነፍ ፕላቲኒየም ስታርስ ከኤምሲ አልጀር ጋር አንድ አቻ ተለያይቷል፡፡ ምባባኔ ስዋሎስ የስዋዚላንድ ሊግን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ላይም ጥንካሬ በዘንድሮው የአፍሪካ ክለቦች ውድድር አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ ፕላቲኒየም ስታርስ ሎንፌድሬሽን ዋንጫ ትኩረት የሰጠ አይመስልም፡፡

የቀኑ ትልቅ ጨዋታ ያለጥርጥር አልጄሪያ ላይ በኤምሲ አልጀር እና ሴፋክሲየን መካከል የሚደረገው ይሆናል፡፡

ምድበ መ

በመጀመሪያ ጨዋታ ነጥብ የጣሉት የጋቦኑ ሞናና እና የደቡብ አፍሪካው ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ሊበርቪል ላይ ይጫወታሉ፡፡ ሞናና በመጀመሪያ ጨዋታ በወቅቱ ቻምፒዮን ቲፒ ማዜምቤ 2-0 ሲሸነፍ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ በሜዳው ከጊኒው ሆሮያ ጋር 2 አቻ ተለያይቷል፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

09፡00 –  ምባባኔ ስዋሎስ ከ ፕላቲኒየም ስታርስ

10፡00 – ሞናና ከ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ

10፡00 –  ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ ከ ክለብ አፍሪካ

03፡00 ሞውሎዲያ ክለብ ደ አልጀር ከ ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን

Leave a Reply