የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኤስፔራንስ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል

 

የ2017 ቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቱኒዝያው ቻምፒዮን ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝን አስተናግዶ ያለ ግብ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ፈፅሟል፡፡ በዘንድሮ የውድድር ዘመን በቻምፒዮንስ ሊጉ ግብ ያለማስተናገድ ሪከርዱንም ወደ 6 አስፍቷል፡፡

ከጨዋታው መጀመር ሰአታት አስቀድሞ ወደ ስታድየሙ ለመግባት ረጃጅም ሰልፎች የነበሩ ሲሆን ጨዋታውም በተጠቀጠቀ ተመልካች እና በሞቀ ድባብ ፊት ተካሂዷል፡፡

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንዳውንስን ከገጠመው ቡድኑ የ3 ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ራምኬል ሎክን በሳላዲን ሰኢድ ፣ ተስፋዬ አለባቸውን በምንተስኖት አዳነ ፣ ደጉ ደበበን በፍሬዘር ካሳ በመተካት በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ጥቂት የግብ እድሎች የተፈጠሩበት ነበር፡፡ በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች በብቸኛ የፊት አጥቂነት የተሰለፈው ሳላዲን ሰኢድን ማዕከል ያደረገው የማጥቃት እንቅስቃሴም ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው ሲከላከሉ በነበሩት የኤስፔራንስ ተከላካዮች ቁጥጥር ስር በቀላሉ ወድቆ ተስተውሏል፡፡

በ14ኛው ደቂቃ ከሰንዳውንስ ጋር በተደረገው ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሮበርት ኦዶንካራ ባጋጠመው ጉዳት በዘሪሁን ታደለ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡

ጨዋታው በኦዶንካራ ጉዳት ምክንያት ከተቋረጠበት ቀጥሎ ባሉት ቀጣይ ደቂቃዎች ጨዋታው እጅግ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ታይቶበታል፡፡ በተለይ ባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጠጋግተው ሲከላከሉ የነበሩት ኤስፔራንሶችን አልፈው ግልጽ የማግባት አጋጣሚ መፍጠር ተስኗቸዋል፡፡

ሙሉ ለሙሉ በመከላከል እና የሜዳውን ስፋት ተጠቅመው አልፎ አልፎ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ኤስፔራንሶች በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጎል ለመሆን የተቃረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ በ45ኛው ደቂቃ ጋሌኒ ቻላሊ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ ዘሪሁን ያወጣበት እንዲሁም ቻላሊ በድጋሚ ከግቡ አቅራቢያ ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት አስደንጋጭ ሙከራ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ኤስፔራንስ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ችለዋል፡፡ በ48ኛው ደቂቃ ሳላዲን ወደ መሀል የተጠጋውን የኤስፔራንስ ተከላካዮች በግሩም ሁኔታ  አምልጦ ወደ ግብ ክልል በመጠጋት ሞከረ ተብሎ ሲጠበቅ ለአዳነ ያመቻችቶ አቀብሎት አዳነ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡፡ በ50ኛው ፣ 52ኛው እና 61ኛው ደቂቃዎች ላይ አብዱልከሪም ንኪማ የሞከራቸው ኳሶችም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሚጠቀሱ የግብ ሙከራዎች ናቸው፡፡

አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለው ጨዋታ 67ኛው ደቂቃ ላይ አኔስ ባድሪ ያሻማውን ኳስ ታሀ ያሲን በግምባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

64ኛው ደቂቃ ላይ ጋሌኒ ቻላሊ በፕሪንስ ላይ በሰራው ከኋላው በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ሆኖም ቀሪዎቹን ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች አጋጣሚውን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ72ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ፕሪንስ በቮሊ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሲያወጣበት ሳላዲን አግኝቶ ሁለት ጊዜ ሞክሮ ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ውጪ ግልጽ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይባስ ብሎ በ84ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከል ባህርይ ያለው ተስፋዬ አለባቸው ተቀይሮ መግባቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ያለመ አድርጎታል፡፡

ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት መፈፀሙን ተከትሎ ኤስፔራንስ በ4 ነጥቦች ምድቡን ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Leave a Reply