በመጪው ሰኔ 3 ወደ ኩማሲ በማቅናት የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ የምድብ ጨዋታውን ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከረፋድ 04:00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጀመርያ ልምምዱን አድርጓል።
ዋልያዎቹ ማረፊያቸውን ካፒታል ሆቴል ያደረጉ ሲሆን ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ትላንት ድረስ ካፍ ባወጣው አዲስ ህግ መሰረት ሁሉም ተጨዋቾች የህክምና ምርመራቸውን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ዛሬ ልምምዳቸውን ጀምረዋል፡፡ በትላንትናው እለትም በካፒታል ሆቴል ጂምናዝየም በመግባት ልምምድ ማደረጋቸው ታውቋል፡፡
በዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና ረዳቶቻቸው ዘሪሁን ሸንገታ እና በለጠ ገ/ኪዳን ፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ፀጋዘአብ አስገዶም ፣ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር አያሌው እና ፊዚዮቴራፒስት ይስሐቅ ሽፈራው በተገኙበት ከአንድ ሰአት በላይ ያህል የፈጀ የልምምድ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡ ቀለል ያለ ፣ ከኳስ ጋር መሰረት ያደረገ የግማሽ ሜዳ የማቀናጀት ጨዋታ እና የትንፈሽ ስራ የልምምድ አካላቸው ነበር።
በልምምዱ ወቅት ጥሪ ከተደረገላቸው 29 ተጨዋቾች መካከል 23 ተጨዋቾች የተገኙ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አስቻለው ታመነ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሳላዲን ሰኢድ ክለባቸው በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ በመሆኑ ፤ ኡመድ ኡክሪ እና ሽመልስ በቀለ ደግሞ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ባለባቸው ጨዋታ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ዘግይተው የሚቀለቀሉ ይሆናል፡፡ ምናልባትም አራቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ክለባቸው በተከታታይ ካለበት ጨዋታ አንፃር ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የመቀላቀላቸው ነገር አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል እየተገመተ ነው ።
ግንቦት 26 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን የሚያደርግ መሆኑ ቢነገርም በማግስቱ ግንቦት 27 ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የዲሪ ኮንጎው ኤኤስ ቪታን የሚያስተናግድ በመሆኑ የፕሮግራም መደራረብ የተፈጠረ ከመሆኑ አኳያ ምናልባት የአቋም መፈተሻው በክልል ከተማ አልያም የቀን ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ለማከናወን ኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥረት እያደረገ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ ከዩጋንዳ ጋር ከሚደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በኋላም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ ማሲ የሚያቀኑትን 18 ተጨዋች ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
* በመጨረሻም
ኤሪያ የትጥቅ አምራች ኩባንያ ለብሔራዊ ቡድኑ የተሟላ የትጥቅ አቅርቦት ለማድረግ ስምምነት ቢኖርም በዛሬው የልምምድ ፕሮግራም የአሰልጣኞች ቡድን አባላት የተለያዩ ትጥቆችን በመልበስ ቡድኑን ሲያሰሩ አስተውለናል፡፡ በቀጣይ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች ወጥ የሆነ ትጥቅ በመልበስ የልምምድ ፕሮግራም ላይ ቢገኙ መልካም ነው እንላለን፡፡