ሀዋሳ ከተማ እና ደደቢት ለኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ፍጻሜ አለፉ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ደደቢት እና ሀዋሳ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት እሁድ ለሚደረገው የፍጻሜ ፍልሚያ አልፈዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማዋ ምርቃት ፈለቀም እለቱን ነግሳበታለች፡፡

08:30 ላይ የተገናኙት በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ በየምድባቸው ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ ነበሩ፡፡ በጨዋታውም ሀዋሳ ከተማ በምርቃት ፈለቀ ሐት-ትሪክ በመታገዝ  5-2 በሆነ ውጤት አዳማን መርታት ችሏል፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር 2 ያክል ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው፡፡ እታለም አመኑ ከቀኝ መስመር ያሻማችውን ቅጣት ምት ትርሲት መገርሳ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ቻለች፡፡ ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች በተመሳሳይ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል በረጅሙ የተሻማውን ኳስ በግብጠባቂዋ እምወድሽ ይርጋሸዋ እና በመሀል ተከላካይዋ ምህረት ተክለልኡል አለመናበብ ተጠቅማ ምርቃት ፈለቀ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡ ምርቃት በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከርቀት አክርራ በመምታት የሞከረችው ኳስ የግቡ ቋሚ ለትማ ልትመለስ ችላለች፡፡

ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በሁለት አጋጣሚዎች ዮዲት መኮንን ከርቀት ሞክራ ወደ ውጪ የወጣችባት እንዲሁም የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ካመከኗቸው ኳሶች በቀር ተጠቃሽ ሙከራዎች ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡፡፡

አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን በቀጠሉበት አጋጣሚ በ45ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ወደ አዳማ የግብ ክልል ተጠግተው ምርቃት ፈለቀ ከጠባብ ቦታ ያገኘችውን ኳስ በቀጥታ በመምታት ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥራ የመጀመርያው አጋማሽ በሀዋሳ 3-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ በ53ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች የአዳማን የተስፋ ጭላንጭል ያከሰመች አራተኛ ግብ በአጥቂዋ ስንታየው ማቴዎስ አማካኝነት ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ለዚህችም ግብ መቆጠር በተመሳሳይ የምርቃት ፈለቀ አስተዋጽኦ የላቀ ነበር፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች የጨዋታው መንፈስ እጅጉን ተቀዛቅዞ ቀጥሎ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ካሰች ፋሳ ከቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳሰ በጨዋታው እጅግ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለችው የጨዋታው ኮከቧ ምርቃት ፈለቀ ተቀይራ የገባችው የአዳማ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ግቧን ለቃ መውጣቷን ተመልክታ በግንቧሯ በመግጨት ለራሷ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ፣ ለቡድኗ አምስተኛውን ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

ቡድኗን ወደ ጨዋታው ለመመለስ በከፍተኛ ደረጃ ጥረት ስታደርግ የነበረችው ናርዶስ ጌታነህ አዳማ ከተማዎች ከባዶ መሸነፍ የዳኑበትን ግብ በ80ኛው ከማስቆጠርም በዘለለ እሷ በመጠለፏ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በ89ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ አስቆጥራ ጨዋታው በ5-2 የሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በ10:30 የተገናኙት ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ደደቢት ነበሩ፡፡ በጨዋታው ደደቢት በአካዳሚ ጠንካራ የመከላከል እንቅስቃሴ ቢፈተንም የኋላ ኋላ 2-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ አካዳሚዎች በመከላከሉ ረገድ ፍፁም የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡ በጥልቀት ወደ ኃላ ተስበው በመጫወት ደደቢቶች ክፍተት እንዳያገኙ ማድረግም ችለው ነበር፡፡ ነገርግን በ36ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ከሶስት የአካዳሚ ተከላካዮች ጋር ታግላ ቡድኗን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ልክ እንደ መጀመሪያ አጋማሽ በደደቢቶች ፍፁም የሆነ የኳስ ቁጥጥርና የግብ መከራ ታጅቦ ተካሂዷል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ኤደን ሽፈራው የመታችው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረችው ሎዛ አበራ በግንባሯ አስቆጥራ ጨዋታው በደደቢት የ2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ በመጪው እሁድ በ10፡00 ፍፃሜውን ሲያገኝ ሀዋሳ ከተማ ከደደቢት ለዋንጫ ይፋለማሉ፡፡

1 Comment

  1. የሎዛ ጎሎች ስንት ደረሱ?? ሪከርድ ሊያዝላት ይገባል..እንደ ዮርዳኖስ የሷም በቀላሉ አይሰበርም። የምንጊዜም ምርጥ..ሎዛ።
    soccerethiopia…እንደ ወንዶቹ የአግቢዎችን ሰንጠርዥ ብታስገቡ ጥሩ ነው። ለሁሉም ግን እናመሰግናለን።

Leave a Reply