ፕሪሚየር ሊግ ፡ መድን መውረዱን አረጋገጠ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ በክልል እና በአዲስ አበባ በተደረጉ ጨዋታዎች መድን ወደ ከፍተኛ ብሄራዊ ሊግ መውረዱን ሲያረጋግጥ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ ተለያይቷል፡፡

አዲስ አበባ ስታዲየም 9፡00 ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን 2-0 ተሸንፏል፡፡ ይህም ውጤት የአስራት ኃይሌውን ቡድን ወደታችኛው ዲቪዥን እንዲወርድ አድርጎታል፡፡ በ2005 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሰው መድን ከ2 የውድድር ዘመናት ቆይታ በኋላ ወደመጣበት ተመልሷል፡፡

ሐረር ላይ ሐረር ቢራ በኢትዮጵያ ቡና ተሸንፎ የመድንን መስመር ሊከተል ተቃርቧል፡፡ የኢትዮጵ ቡናን የድል ግብ መስኡድ መሃመድ አስቖጥሯል፡፡

አሰላ ላይ መብራት ኃይል ሙገር ሲሚንቶን አሸንፎ ከመውረድ ስጋት እፎይታን አግኝቷል፡፡ የመብራት ኃይልን የማሸነፍያ ግቦች በረከት ይስሃቅ እና አዎይኒ ሚካኤል ከመረብ ሲያሳርፉ ‹‹ የማይዘሙት ምሰሶዎች ›› ደረጃቸውን አሻሽለው ወደ 10ኛ ከፍ ብሏል፡፡

ጎንደር ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ ካለ ግብ አቻ ሲለያይ ፣ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው አርባምንጭ ከነማም በተመሳሳይ ካለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በ11፡30 ሲጠበቅ የነበረው በአምናው እና በዘንድሮው ቻምፒዮን መካከል የተደረገው ፍልሚያ 3-3 አቻ ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው በፊት 5 ጨዋታ እየቀረው የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት ተጫዋቾች በጭብጨባ እና አበባ ስጦታ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት እየመራ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪም ‹‹ ከማን አንሼ ›› በሚገኙ ደጋፊዎች የማስታወሻ ስጦታ ተበርልቶለታል፡፡

ጨዋታው በበርካታ ሙከራዎችእና ግቦች የታጀበ ሲሆን ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአዳነ ግርማ አማካኝነት ነው፡፡ ከአዳነ ግብ በኋላ ደደቢት በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች መስፍን ኪዳኔ ግብ አቻ ሆነው የመጀመርያው አጋማሽ በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስ በደደቢቱ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ስህተት የተገኘችውን አጋጣሚ ሳላዲን በርጊቾ ወደ ግብነት ቀይሮ 2-1 የመምራት አጋጣሚ ቢያገኙም ብዙም ሳይቆይ ሚካኤል ጆርጅ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋን ስህተት ተጠቅሞ ደደቢትን አቻ አድርገዋል፡፡ ከግቡ በኋላ ተደጋጋሚ ጫና መፍጠር የቻሉት ደደቢቶች በታደለ መንገሻ ግብ 3-2 መምራት ሲችሉ በዳኞች አለመግባባት የተፈጠረ መልካም የግብ ማግባት እድል ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ከማእዘን የተሸገረውን ኳስ አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሽንፈት የታደገች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ59 ነጠቦች ሲመራ ኢትዮጵያ መድን በ10 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ኡመድ ኡኩሪ (14) እና ፍፁም ገብረ ማርያም (10) የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ይመራሉ፡፡

ያጋሩ