‹‹ (በዛምቢያው ጨዋታ) ሜዳው ውስጥ ከምጫወተው ይልቅ የማወራው በልጦ ነበር ›› በኃይሉ አሰፋ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ድንቅ የመስመር አማካይ በኃይሉ አሰፋ ተጫዋቾቹን ወክሎ በትላንትናው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ 2ኛ አምበል በእለቱ ከተናገራቸው መካከል አንኳር አንኳሩን መርጠን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ስለ ዝግጅታቸው

“በፍላጎት እየተዘጋጀን ነው፡፡ እዚህ ከመጣን ሳምንት ሊሞላን ነው፡፡ ሁሉም ነገር በጥሩ መንገድ እየተካሄደ ነው፡፡ ለአንድ ቡድን ውጤታማነት ዋናው መሰረት አንድነት ነው፡፡ በቡድኑ ውስጥ ያለው አንድነት እና ፍቅር ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየን ተጫዋቾች ከአዳዲሶቹ ጋር ያለን ግንኙነት መልካም ነው፡፡”

ስለ ባህርዳር

“የባህርዳር ስታድየም ካለጥርጥር ከአዲስ አበባ ስታድየም በብዙ መልኩ የተሸለ ነው፡፡ እዚህ ስመጣ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ሜዳው አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ለጨዋታ በጣም ምቹ ነው፡፡”

ስለ አምበልነቱ

“ከዛምቢያ ጋር የተደረገው ጨዋታ ብሄራዊ ቡድኑን በአምበልነት የመራሁበት የመጀመርያ ጨዋታ ነበር፡፡ በክለብ ደረጃ ብዙ ጨዋታዎች ላይ አምበል ሆኜ ብገባም የብሄራዊ ቡድን ኃላፊነት ከባድ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጨዋታው የተሰለፉት አብዛኛዎቹ ተሰላፊዎች የብሄራዊ ቡድኑን ማልያ ለመጀመርያ ጊዜ የለበሱ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ሜዳው ውስጥ ከምጫወተው ይልቅ የማወራው በልጦ ነበር፡፡ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ጫና ውስጥ ስለሚከት ተጫዋቾቹን በማረጋጋት እና በማነቃቃት ኃላፊነት ተጠምጄ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በጨዋታው የሚጠበቅብኝን እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻልኩም፡፡”

ስለ አሰልጣኞቹ

“በብሄራዊ ቡድኑ በተለያዩ አሰልጣኞች ስር አሳልፌያለሁ፡፡ በሰውነት ዘመን ቡድኑ ውጤታማ የነበረ በመሆኑ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ በባሬቶ ዘመን ደግሞ ከጨዋታው ፍልስፍና ጋር ልጣጣም ባለመቻሌ ከቡድኑ ውጪ አድርጎኝ ነበር፡፡”

ያጋሩ