የጨዋታ ሪፖርት | አፄዎቹ 2-0 ከመመራት ተነስተው ከቻምፒዮኖቹ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መጋቢት 10 እንዲካሄድ መርሃ ግብር ወጥሎት የነበረውና ቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረበት አህጉራዊ ውድድር በተስተካካይ ጨዋታነት ተይዞ የነበረው የ19ኛ ሳምንት የፈረሰኞቹ እና አፄዎቹ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዶ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው ማክሰኞ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ጋር አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ ምንተስኖት አዳነ እና አስቻለው ታመነ በቀር የ9 ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በውድድር ዘመኑ እምብዛም የመሰለፍ እድል ያላገኙትን ተጫዋቾችን በመጠቀም በሚታወቁበት የ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ ፋሲሎች በበኩላቸው እንደነዮሀንስ ሽኩር ፣ ያሬድ ባየህ ፣ አብዱረህማን ሙባረክ  እንዲሁም ኤደም ሆሮሶውቪ የመሳሰሉ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾችን በተለያየ ምክንያት ሳይዙ በተመሳሳይ የ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች እየቀራቸው በ55 የሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን የፋሲል ከተማ ተጫዋቾች በሁለት ረድፍ ተከፍለው በጭብጨባ አጅበው ወደ ሜዳ አስገብተዋቸዋል፡፡

ጨዋታው ከተጀመረ ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ በግምት ከፋሲል የግብ ክልል በ25 ሜትር ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት ራምኬል ሎክ ዶንግ በቀጥታ በመምታት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ፋሲል ከተማን ከሰበታ ከተማ የተቀላቀለው ወጣቱ ግብጠባቂ ምንተስኖት አድጎ ስህተት ታክሎባት የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ግብ ሆና ተቆጥራለች፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ፋሲል ከተማዎች ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ኳሶችን መስርተው ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም ፊት መስመር ላይ ያሉት አጥቂዎቹ በሰፊ ርቀት ከቡድኑ ቀሪ ተጫዋቾች በመነጠላቸው ተመስርተው የሚመጡት ኳሶች ውጤታማ አልነበሩም፡፡ ይሀህ እንቅስቃሴ እምብዛም ውጤታማ አለመሆናቸውን የተረዱት ፋሲሎች በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን በቀጥታ ወደፊት ለመጣል ጥረት አድርገዋል ፤ ይህም ሂደት በተደጋጋሚ በጨዋታው የቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ደካማ ጎናቸው በነበረው የግራ መስመር በኩል በተደጋጋሚ የፋሲሉ የቀኝ መስመር አጥቂ ናትናኤል ጋንቹላ በተደጋጋሚ  ተሻጋሪ ኳሶችን ቢያገኝም ኳሶቹን ወደ መሀል ለማቀበል የሚያደርገው ጥረት በቀላሉ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ሊቋረጥበት ችሏል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ከፋሲሎች የሚሰነዘርባቸውን ጥቃቶች በመከላከል በኩል ጠንካራ የነበሩ ቢሆንም ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ግን በጣም ደካማ ነበር፡፡ ሆኖም ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ መግባት የቻለው ብሩኖ ኮኔ በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲጥር ተስተውሏል፡፡

በ36ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃ ፈረሰኞቹ ያገኙትን አጋጣሚ ብሩኖ ኮኔ በግሉ ከሶስት የፋሲል ተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ፋሲል የግብ ክልል ከደረሰ በኃላ ማራኪ የሆነችን ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 2-0 ማሳደግ ችሏል፡፡ ይህችም ግብ ለቡርኪናፋሷዊው አጥቂ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት አርባምንጭ ላይ ካስቆጠራት ግብ በኃላ በሊጉ ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ሆናለች፡፡

ፋሲል ከተማ በዛሬው ጨዋታ ላይ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ለወትሮው ይታወቁበት የነበረው ፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች በኩል ደከም ብለው ተስተውለዋል፡፡ በዚሁ አጋማሽ ፋሲሎች ወደ ግብ ካደረጓቸው ሙከራዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የሚሞከሩና በአመዛኙ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ፡፡

በ40ኛው ደቂቃ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ሙሉ ትኩረታቸውን በማጥቃት ላይ አድርገው በቁጥር በርከት ብለው በፋሲል የግብ ክልል ውስጥ ይገኙ በነበረበት ወቅት ፋሲሎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ደደቢትን ለቆ በውሰት ውል ፋሲል የተቀላቀለው አቤል ያለው ወደ ግብ ቢሞክርም አስቻለው ታመነ እንደምንም ብሎ ከግቡ መስመር ላይ ያወጣበት ኳስ በፋሲሎች በኩል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡

በጨዋታው ላይ እንደወትሮው ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እጅግ ባማረ መልኩ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል፡፡ በተመሳሳይ በስታድየሙ የቀኝ ወገን የነበሩት የፋሲል ደጋፊዎች ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር አንድ ላይ በመሆን ቡድናቸውን አበረታተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረዘም ላሉ ሳምንታት ከቡድኑ ጋር በጉዳት አብሮ ያልነበረውን በኃይሉ አሰፋን በአቡበከር ሳኒ ቀይሮ ሲያስገባ በፋሲል ከተማ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያደረገው ሰለሞን ገ/መድህን ወጥቶ ኤፍሬም አለሙ ተክቶት ገብቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እጅጉን ተቀዛቅዘው ተስተውለዋል፡፡ በአንጻሩ በፋሲል ከተማዎች በኩል ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኤፍሬም አለሙ የጨዋታውን መንፈስ ሙሉ ለመሉ ቀይሮታል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከኤፍሬም መግባት በኃላ ከቡድኑ ተነጥለው የነበሩትን ሶስቱን የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ከቀሪው ቡድን ጋር በማገናኘት እንዲሁም ፋሲሎች በሚታወቁበት ፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች ላይ ዋንኛ ተዋናይ ነበር፡፡

በ55ኛው ደቂቃ ፋሲሎች በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ  የነጠቁትን ኳስ በፈጣን ሽግግር ከሄዱ በኃላ አቤል ያለው ከግራ የፈረሰኞቹ ሳጥን ወደ መሀል ሰብሮ በመግባት ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ኤርሚያስ ሀይሉ አቀብሎት ኤርሚያስ በቀላሉ ደገፍ አድርጎ በማስቆጠር የጨዋታውን መንፈስ የቀየረችውን የፋሲልን የመጀመሪያ ግብ ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ፋሲሎች በተደጋጋሚ ጫና ፈጥረው በመጫወት ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል በ57ተኛው እንዲሁም በ61ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ያደረጋቸው ሙከራዎች ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን አጋጣሚ በሀይሉ አሰፋ ወደ መሀል ሰብሮ በመግባት ከፋሲል የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ የሞከራትን ኳስ ምንተስኖት እንደምንም አድኗት የተመለሰችውን ኳስ የፋሲል ተከላካዮች ብሩኖ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በማለት በመዘናገታቸው በድጋሚ ብሩኖ ኮኔ ያገኛትን አጋጣሚ በድጋሚ ሞክሮ አሁንም እንደገና የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ያዳነበት በፈረሰኞቹ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ የተደረገች አስደንጋጭ ሙከራ ነበረች፡፡ ከዚች ሙከራ በደቂቃዎች ልዩነት ብሩኖ ኮኔ ባጋጠመው ጉዳት በመሀሪ መና ከሜዳ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ወደ ጨዋታው ለመመለስ እጅግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ፋሲሎች በ77ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ውስጥ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ኤፍሬም አለሙ አግኝቶ ከግቡ አናት በላይ የሰደዳት ሙከራ ፋሲሎች አቻ ለመሆን ይችሉባት የነበረች አጋጣሚ ነበረች፡፡

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደበት ወቅት በ82ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ አቤል ያለው በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ውስጥ በአስቻለው ታመነ በተሰራበት ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ከድር ኸይረዲን በማስቆጠር አፄዎቹን ከመመራት ተነስተው አንድ ነጥብ ተገርተው እንዲወጡ አስችሏል፡፡

ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አዳነ ግርማ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት በመሩት አልቢትር ላይ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡

በውጤቱ መሠረት የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ5 ተከታታይ ድሎች በኋላ ነጥብ በመጣል በ56 ነጥቦች ሊጉን ሲመራ ፋሲል ከተማ የደረጃ ለውጥ ሳያስመዘግብ በ42 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *