በመቐለ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲስፕሊን ኮሚቴ ያስተላለፈው ውሳኔ

(ዜናው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተላከ ነው)

ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓ.ም መቐለ ከተማ ከባህርዳር ከተማ የከፍተኛ ሊግ ሁለተኛው ዙር 23ኛው ሣምንት የእግር ኳስ ጨዋታቸውን ባደረጉበት ዕለት ጨዋታው ሊፈፀም 16 ደቂቃ ሲቀረው የተቋረጠ ስለመሆኑ ከጨዋታ አመራሮች የቀረበውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ፤ በተጨማሪም የዕለቱን ኮምሽነር እና ዋና ዳኛ በመጥራት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ የዲስፒሊን ኮሚቴ ማብራሪያ እንዲሰጡ በማድረግ ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ኮሚቴው የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

1ኛ. መቐለ ከተማን በተመለከተ

ከባህርዳር ከተማ ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ደጋፊዎች ጨዋታ እየተካሄደ ወደ ሜዳ በመግባታቸውና ከተጫዋቾች ጋር በመደባደባቸው፤ ለጨዋታው መቋረጥመ የቡድኑ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መግባት ሆኖ በመገኘቱ የመቐለ ከተማ ቡድን በኢ.እ.ፌ ዲስፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 100‚000.00 (መቶ ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡ በተጨማሪ ለደጋፊዎቻቸው በ20 ቀናት ጊዜ ውስጥ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት አስተምረው ሪፖርት ለኢ.እ.ፌ ጽ/ቤት እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡

 

2ኛ. ባህርዳር ከተማን በተመለከተ፡-

2.1 የትጥቅ ቁጥር 16 የመታወቂያ ቁጥር 0756 ተጨዋች ኪዳኔ ተስፋዬ በጨዋታ ላይ በመጐዳቱ ለመጀመሪያ እርዳታ እንዲያገኝ በስትሬቸር በቀይ መስቀል ሙያተኞች ከሜዳ እንዳወጡት ጥፋት የተፈፀመበት ስለመሆኑ ከጨዋታ አመራሮች ተረጋግጧል፡፡ ምንም እንኳን ጥፋት ፈፅሟል ተብሎ ሪፖርት ቢደረግበትም ጥፋቱን ሊፈፅም የቻለው ቃሬዛ ያዥች በፈፀሙበት ጥፋት ምክንያት መሆኑ ታውቋል:: ስለዚህ የችግሩ ምክንያት ነው ተብሎ ቢቀርብም ያለምንም ቅጣት እንዲታለፍ ተወስኗል፡፡

2.2 ተጨዋች ኩማ ደምሴ የትጥቅ፣  ቴዎድሮስ ሙላት፣  ሚኪያስ ግርማ፣  ተስፋሁን ሸጋው፣ የተባሉት ተጨዋቾች የመቐለ ከተማ ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ውስጥ በመግባት በፈጠሩት ግርግር (ረብሻ) ምክንያት ራሳቸውን በመከላከል ውስጥ ሆነው ጥፋት የፈፀሙ ስለመሆኑ ከጨዋታ አመራሮች ሪፖርት የተደረገ በመሆኑ ኮሚቴው ጉዳዮን በጥልቀት መርምሮ ያለምንም ቅጣት እንዲታለፋ ወስኗል፡፡

2.3 ዘውዱ መስፍን እና ተዘራ መንገሻ የተባሉት ተጨዋቾች የቀይ መስቀል ዕርዳታ ሙያተኞችን በመደብደብ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የሆነ ተግባር መፈፀማቸው ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ሁለት ተጨዋቾች በኢ.እ.ፌ ዲስፕሊን መመሪያ መሠረት እያንዳንዳቸው 4 /አራት/ ጨዋታ እና ብር 4‚000.00 (አራት ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲከፈሉ ተወስኗል፡፡

2.4 አቶ ጥጋቡ አብተው የባህርዳር ከተማ የቡድን መሪ:-የዕለቱ ዳኞች ኃላፊነታቸውን በነፃነት እንዳይወጡ በቡድን ላይ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ተጨዋቾችን በማስተባበር አናስመታም በማለታቸው፤ ዳኞች ሌቦች፣ ጉበኞች በማለት የተሳደቡ ስለመሆኑ የተረጋገጠባቸው በመሆኑ ፤የቡድናቸው መሪ እንደመሆናቸው በአርአያነት መታየት ሲገባቸው ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ በመሆን ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲስፕሊን መመሪያመሰረት 5 /አምስት/ ጨዋታ እንዲታገዱ እና ብር 4‚000.00 ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡

2.5 አቶ በቀለ መንግስት፡- የቡድን ወጌሻ በቦታው የነበሩትን የቀይ መስቀል ዕርዳታ ሰጭዎችን የተደባደቡ ስለመሆኑ በቀረበባቸው ሪፖርት እና በተደረገው ማጣራት የተረጋገጠ ስለሆነ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ በመሆን ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲስፕሊን መመሪያ መሠረት ጨዋታ እንዲታገዱ እና ብር 4‚000.00 (አራት ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡ የተወሰነባቸውን የቅጣት ገንዘብ የተወሰነው ጊዜ እስከሚከፍሉ ድረስ ፌዴሬሽኑ ከሚመራው እግር ኳስ ውድድር በኢ.እ.ፌ ዲስፕሊን መመሪያ መሰረት እንዳይሳተፉ ተወስኗል፡፡

3ኛ. ሁለቱን ቡድኖች በተመለከተ:-የመቐለ ከተማ እና የባህርዳር ከተማ ቀሪ የጨዋታ ጊዜ ያለተመልካች በዝግ ስታዲየም እንዲጫወቱ ተወስኗል፡፡  የጨዋታው ቀንና ሰዓት በከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ይወሰናል፡፡

 

-የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን-

Leave a Reply