ኮንፌድሬሽን ዋንጫ | ኬሲሲኤ ፣ ምባባኔ ስዋሎስ እና ኤምሲ አልጀር አሸንፈዋል

የካፍ ኮንፌድሬሽንስ ዋንጫ አራት የምድብ ጨዋታዎች ማክሰኞ ሲደረጉ ኬሲሲሰኤ ፣ ምባባኔ ስዋሎስ ፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ኤምሲ አልጀር ድል ቀንቷቸዋል፡፡

 

ምድብ ሀ

ኬሲሲኤ ከኃላ ተነስቶ ክለብ አፍሪካን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ፊሊፕ ኦሞንዲ ስታዲየም ላይ በተደረገው ጨዋታ የቱኒዙ ክለብ አልጄሪያዊው ሙክታር ቤልኬቲር ከሳጥኑ ውጪ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ የመጀመሪያው 45 መገባደጃ ላይ ዴሪክ ኒስምባቢ ከደኒስ ኦኮት የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አቻ ኬሲሲኤ አቻ አድርጓል፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ቶም ማሲኮ የማሸነፊዋን ግብ በድንቅ ሁኔታ አክርሮ በመምታት ከመረብ አዋህዷል፡፡

ዛሬ ሪቨርስ ዩናይትድ ፉስ ራባትን ያስተናግዳል፡፡ ምድቡን አሁንም ፉስ ራባት ሲመራ ክለብ አፍሪካ እና ኬሲሲኤ በግብ ክፍያ ተበልጠው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው፡፡

 

ምድብ ለ

በሜዳቸው የተጫወቱት ምባባኔ ስዋሎስ እና ኤምሲ አልጀር ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ምባባኔ ስዋሎስ ፕላቲኒየም ስታርስን 4-2 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ለስዋዚላንዱ ክለብ ሳቤሎ ንዲዚንሳ አራቱንም ግቦች ሲያስቆጥር ቤንሰን ሺሎንጎ የደቡብ አፍሪካው ክለብን ከሽንፈት ያልታደጉ ሁለት ግቦችን በፍፁም ቅጣት ምት መረብ አሳርፏል፡፡

ኤምሲ አልጀር አልጀርስ ላይ ሴፋክሲየንን 2-1 ረቷል፡፡ የአልጀርሱን ክለብ የድል ግቦች ሂሻም ኔካች እና አብድራማን ሀቾድ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ለቱኒዚያው ክለብ ካሪም አዎዲ ከሽንፈት ያለታደገች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ኤምሲ አልጀር በአራት ነጥብ ሲመራ ምባባኔ ስዋሎስ ሴፋክሲየንን በግብ ክፍያ በልጦ በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡

 

ምድብ መ

ስምንት ግቦች በታዩበት ጨዋታ የደቡብ አፍሪካው ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ሞናናን 5-3 አሸንፏል፡፡ ሱፐርስፖርት በግራንት ኬካና ቀዳሚ ሲሆን አብዱ አትቻቦ ሞናናን በ27ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል፡፡ ታቦ ምናያማኒ አከታትሎ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የመጀመሪያው አጋማሽ በሱፐርስፖርት 3-1 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የጋቦኑ ክለብ ሁለት ግዜ የፍፁም ቅጣት ምቶች አምክኗል፡፡ ጀርሚ ብሮኪ ሁለት ግቦችን ለሱፐር ስፖርት ሲክል ሃሚዱ ሲናዮኮ እና ሉዊስ አሜካ ለሞናና ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል፡፡

ዛሬ የጊኒው ሆሮያ ቲፒ ማዜምቤን ያስተናግዳል፡፡ ምድቡን ሱፐርስፖርት ዩናይትድ በአራት ነጥብ ይመራል፡፡

 

የማክሰኞ ውጤቶች

ምባባኔ ስዋሎስ 4-2 ፕላቲኒየም ስታርስ

ሞናና 3-5 ሱፐርስፖርት ዩናይትድ

ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ 2-1 ክለብ አፍሪካ

ሞውሎዲያ ክለብ ደ አልጀር 2-1 ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን

 

የዛሬ ጨዋታዎች

16፡00 – ሆሮያ ከ ቲፒ ማዜምቤ

16፡00 – ሪቨርስ ዩናይትድ ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት

18፡00 – ስሞሃ ከ ክለብ ሬክሪቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ

21፡00 – አል ሂላል ኦባያድ ከ ዜስኮ ዩናይትድ

Leave a Reply