ቻምፒየንስ ሊግ | ሩዋንዳዊያን ዳኞች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤኤስ ቪታን ይመራሉ

በቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሶስተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዲ.ሪ. ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብን ያስተናግዳል፡፡ ፈረሰኞቹ በመጪው እሁድ ለሚያደርጉት የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ካፍ ሩዋንዳዊያን ዳኞች መርጧል፡፡

እሁድ 10፡00 የሚደረገው ወሳኝ ጨዋታ በመሃል ዳኛነት የሚመራው ሉዊ ሃኪዚማና ሲሆን በረዳትነት ቲዮጌን ንዳጂማና እና አምብሮይስ ሃኪዚማና ሆነዋል፡፡ ከ2012 ጀምሮ የፊፋ ዋና ዳኛ የሆኑት ሃኪዚማና ሩዋንዳ ካሏት አምስት የፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኞች መካከል አንዱ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ ኢንተርናሽናል ዳኛ ናቸው፡፡ ረዳቶቹ ንዳጂማና እና ሃኪዚማና ሩዋንዳ ካሏት ሰባት ረዳት ዳኞች መካከል ናቸው፡፡

የ38 ዓመቱ ሃኪዚማና በቅርቡ ዛምቢያ አዘጋጅታ እሯሷ ባሸነፈችው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ በምድብ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ከሴኔጋል እንዲሁም በግማሽ ፍፃሜው ሴኔጋል ከጊኒ ያደረጉት ጨዋታ መርቷል፡፡ በ2016 ቻምፒየንስ ሊግ በማጣሪያ ዙሮች የጋቦኑ ማንጋ ስፖርት ከቱኒዚያው ኤትዋል ደ ሳህል እንዲሁም ሌላኛው የቱኒዚያ ሃያል ክለብ ክለብ አፍሪካ የ2016 ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ተፋለሚ የነበረው እና ከአልጄሪያ ሊግ 1 ሞቢሊስ ዘንድሮው የወረደው ኤምኦ ቤጃያ ጨዋታ መምራት ችሏል፡፡ ዋና ዳኛው ከዚህ ቀደም በሴካፋ 2013 ዋንጫ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን በዮናታን ከበደ ብቸኛ ግብ 1-0 እና ዛንዚባርን 3-1 በፋሲካ አስፋው፣ ሳላዲን በርጌቾ እና ዩናታን ከበደ ግቦች 3-1 ረታችባቸውን ጨዋታዎች በዋና ዳኝነት መርተዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት የቻምፒየንስ ሊጉ የምድብ ጨዋታዎች ያለግብ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ኤስፔራንስ ጋር አቻ ሲለያይ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኤኤስ ቪታ ክለብ በሁለቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁኔታ 3-1 ሽንፈትን ቀምሷል፡፡ በኮንጎ ሊና ፉት የመጨረሻ ዙር ጨዋታ ሳንጋ ባላንዴን ባሳላፍነው እሁድ 2-0 በመርታት በሊጉ ከዲሲ ሞቴማ ፕምቤ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በ15 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡

1 Comment

  1. st gorge beaten As vita but still soccer Ethiopia remain silent to narrate the news, game statistics and about the beautiful st George fans who supported their team an astonishing and colorful way that has never been seen before. could you tell me the reason behind your silence?

Leave a Reply