ካፍ በአዲስ አበባ ስታድየም የመጫወቻ ሜዳ ዙርያ ፌዴሬሽኑን አስጠነቀቀ

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽንን በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ላይ ያለውን ቅሬታ አሰምቷል፡፡ ኮንፌድሬሽኑ ከዚህ ቀደምም ስታዲየሙ መሻሻል እንደሚገባው በዚሁ አመት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ጋር ካደረጉት የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በኃላ እንግዳው ቡድን በሜዳው ጥራት ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡ ስታዲየሙ ማንኛውንም የአህጉራዊ ጨዋታዎች እንዳያስተናግድ እገዳ ተጥሎበታል ቢባልም ሶከር ኢትዮጵያ ከካፍ እንዳረጋገጠው ከሆነ ስታዲየሙ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ አለመታገዱን ነው፡፡ ይልቅም ካፍ በመጫወቻ ሜዳው ላይ ፌድሬሽኑ አስፈላጊውን ክትትል እና ስራ እንዲሰራ አሳስቧል፡፡ በመጪው እሁድ በምድቡ ሶስተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ እንደሚካሄድ ካፍ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ለረጅም አመታት የኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ደረጃውን የጠበቀ ጥገና ሳይደረግበት ቆይቷል፡፡ ስታዲየሙ በዘንድሮው የውድድር አመት ለስድስት የአዲስ አበባ ክለቦች የሜዳ ላይ ጨዋታ ያስተናገደ ሲሆን የአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ለጥገና መዘጋቱን ተከትሎ የጨዋታ መደራረብ በስታዲየሙ አጋጥሟል፡፡ ክረምት በገባ ቁጥርም ሜዳው ለጨዋታ አስቸጋሪ ሲሆን ይታያል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *