‹‹ የማሸነፍ ፍላጎት ለድል አብቅቶናል ›› ዮሃንስ ሳህሌ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ . .

‹‹ በመጀመርያው አጋማሽ በምንፈልገው ደረጃ እንዳልተንቀሳቀስንና ከ100 ሺሀ የማያንስ ህዝብ እንዳያዝንብን ተነጋግረን ገብተናል፡፡ ኳሶችን በብዛት ወደግብ ማድረስ እንደሚገባን ተመካክረን ገብተናል፡፡ ከሌሶቶ ተከላካየች ጀርባ ኳሶን ቶሎ ቶሎ በመጣል ጫና መፍጠር ችለናል፡፡ የተጫዋቾቹ የማሸነፍ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ግቦች አስቆጠረን ለማሸነፍ በቅተናል፡፡

‹‹ 4-1-3- 2 ነው የተጫወት ነው፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ በተከላካይ እና አጥቂ መስመራችን መካከል ሰፊ ርቀት ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የሳላዲን እና ጌታነህ እንቅስቃሴ እንዳሰብነው አለመሆን አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ከእረፍት በኋላ ይህንን ክፍተት ማጥበባችን እና በአንድ የፊት አጥቂ ተጫውተን ባዬን ከጀርባው በማድረግ ክፍተቱን መድፈን ችለናል ፡፡ ይህም ግቦች እንድናስቆጥር አድርጎናል፡፡ ከዛ ውጪ ሜዳ ላይ ለመተግበር ያቀድነው 4-1-3-2 ነበር፡፡ አሰላለፉ ዋጋ አላስከፈለንም፡፡ ዋጋ ያስከፈለንና ግብ እንዲቆጠርብን አስተዋፅኦ ያደረገው የተከላካዮች ስህተት ነው፡፡

ስለ ድሉ

‹‹ የማሸነፋችን ዋነኛ ምክንያት ህዝቡ ነው፡፡ የህዝቡ ብዛት በጨዋታው መጀመርያ በተጫዋቾቹ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሮ ነበር፡፡ እየለመዱት ሲመጡ ግን የበለጠ አነቃቅቷቸዋል፡፡ በእረፍት ሰአት የተነጋገርነውም ይህንን ህዝብ ማሳፈር እንደሌለብን ነበር፡፡

‹‹ በግል ደረጃ ለድላችን አስተዋፅኦ አድርጓል ብዬ የምጠራው ተጫዋች የለም፡፡ ከእረፍት በኋላ እንደ ቡድን ተነሳስተን ተጫውተናል፡፡ ማሸነፋችን የ11ዱም ተጫዋች ውጤት ነው፡፡ ››

ስለ ተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ . . .

‹‹ ጌታነህን እንደጠበቅነው እንዳይንቀሳቀስ ያደረገው የአካል ብቃት ችግር ሳይሆን ከቡድኑ ጋር አለመዋሃዱ ነው፡፡ ከነበረው አጭር ጊዜ አንፃር ጌታነህ እና ኡመድን ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር የማቀናጀት ስራ ብዙ አልሰራንም፡፡ በማጥቃት ወረዳው ላይ ኳሶች ይበላሹብን ነበር፡፡

‹‹ ሜዳ ውስጥ ከነበሩት ተጫዋቾች ውስጥ በዛምቢያው ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው ዘካርያስ በህዝቡ ብዛትና ድባብ ተረብሾ ነበር፡፡ እንደ ዘካርያስ ካለ ወጣት ተጫዋች ሁሉንም ነገር በአንድ ላይ መጠበቅ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእረፍት በኋላ ተረጋግቶ ወደ ጥሩ አቋሙ ተመልሷል፡፡ ከሳላዲን የጠበቅነውን አግኝተናል፡፡ በጨዋታው አብዛኛውን ሰአት ቆሞ ቢያሳልፍም ወሳኟን ግብ አስቆጥሯል፡፡ የአንድ ትልቅ አጥቂ ብቃትም ይህ ነው፡፡

‹‹ ሳላዲን እና ዘካርያስ በጊዮርጊስ ፣ አስቻለው እና ስዩም በደደቢት አብረው ስለሚጫወቱ ከጊዜ አንፃር የተከላካይ መስመሩን ለማዋሃድ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ልንጠቀምበት ሞክረናል፡፡ ከዛምቢያ ጋር ስንጫወት ስህተቶች የተፈጠሩት 4 የማይተዋወቁ ተጫዋቾች አንድ ላይ በመሰለፋቸው ነበር፡፡ ፊት መስመር ላይም ሳላዲን እና ጌታነህ ብዙ ጊዜ አብረው ስለተጫወቱ ነው አንድ ላይ ያሰለፍናቸው፡፡ ››

ለሌሴቶ ዝቅተኛ ግምት ስለመሰጠቱ . . .

‹‹ ሌሶቶዎች 5 ወር ተዘጋጅተዋል፡፡ ሳላዲን ከኛ ጋር 2 ቀን ብቻ ነው የተለማመደው ፡፡ ሌሎቹ ከውጭ የመጡትም ከሰኞ ጀምሮ ነው የተለማመዱት ፡፡ ሌሴቶዎች ግን ብዙ ወራት በመዘጋጀታቸው ኮንዲሽናቸው ጥሩ ነበር፡፡ የተደራጀ ቡድን ይዘው እንደሚመጡ ጠብቀን ነበር፡፡ ይህንን ነገርም በሜዳ ላይ አይተነዋል፡፡ በተለይም ያለኳስ የነበራቸው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፡፡ ከእረፍት በፊት እንዲበልጡን ያደረጋቸው መግባባታቸው ነው፡፡ በሚድያ የተባለው እኛ 9 እና 10 እንደምናገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ሜዳ ላይ ያየነው ሌላ ነው፡፡ ከሲሸልስ እና ሌሶቶ በቀላሉ 12 ነጥብ እንደምናገኝ ሁሉ የገመተ ነበር፡፡ ነገር ግን 3 ነጥብ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ››

ከሌሶቶ የተማሩት ነገር . . .

ከሌሶቶ ተማርነው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ከራሳችን የተማርነው ብዙ ነገር አለ፡፡ በእረፍት ሰአት ነገሮች የተለወጡት ከስህተታችን ስለተማርን ነው፡፡ የጨዋታውን ቪድዮ እየተመለከትን ክፍተቶቻችንን ለማረም እንሰራለን፡፡

ያጋሩ